ከ120 አመት በፊት በእጅ የተጻፈ ታሪክ ታትሞ ለንባብ በቃ

68
መቐለ ህዳር 5/2012   ከ120 ዓመታት በፊት በእጅ ተጽፎ በጣሊያ አገር የነበረ ሰነድ ወደ አገሩ ተመልሶና በመፅሀፍ ደረጃ ታትሞ ለንባብ መብቃቱን የትግራይ ባህል ማህበር ገለፀ ።
  ከ120 ዓመት በፊት በደብተራ ፍስሃጊዮርጊስ ዓብየዝጊ በእጅ የተፃፈው ታሪካዊ ሰነድ ከጣሊያን አገር ወደ አገሩ ከተመለሰ 10 ዓመት ቢሆነውም በቅርቡ በመፅሀፍ ደረጃ ታትሞ ትናንት ተመርቋል ። የትግራይ ባህል ማህበር ዋና ዳሬክተር አቶ ብርሀኑ ወልደሚካኤል በምረቃው ስነ ስርዓት ላይ እንደተናገሩት በእጅ የተፃፈው ሰነድ በትግርኛ ቋንቋ የተዘጋጀ ነው ። የመፅሃፉ ዋናይዘት በትግራይ የቀደምት ስልጣኔ፣ ንግሰተ ሳባ ከተለያዩ አገራት የነበራትን የንግድ ግንኝነትና ተያያዥ የኢትዮጵያ ታሪክን የሚዳስስ ነው ብለዋል ። 150 ገፅ ያለው ይኽ መጽሀፍ ለታሪክ ጥናት  ከፍተኛ ፋይዳ እንዳለው ዳሬክተሩ ገልፀው ለመጀመሪያ ጊዜ ከአንድ ሺህ በላይ ቅጂ ታትሞ ለአንባቢው ተደራሽ ማድረግ ተችሏል ። ይኽው ደብተራ ፍስሀጊዮርግስ በእጅ ተፅፎ በባእድ አገር የኖረው ሰነድ እንደ አውሮፓዊያን አቆጣጠር በ1987 በጣሊያን አገር ናፖሊ በተባለ ኢንስቲትዩት አማካኝነት በፕሮፌሰር  ያቆብ  በየነ በጣሊያንኛ ቋንቋ  ታትሞ እንደነበርም አቶ ብርሃኑ ተናግረዋል ። የትግራይ ባህል ማህበር የቦርድ ሰብሳቢ ፣ የትግራይ ቋንቋዎች አካዳሚ ዳይሬክተርና የቋንቋና ባህል ሙሁር ዶክተር ዳንኤል ተክሉ እንደገለፁት ለመጪው ትውልድ እውነተኛውን ታሪክ ማውረስ የሚቻለው ትናንት የተሰራውን ሀቅ በፅሁፍ ከትቦ በማቆየት መሆኑን አስረድተዋል ። በምረቃው ስነ ስርዓት ላይ የተገኘው ጋዜጠኛና ደራሲ አቤል ጉዕሽ በበኩሉ መፅሃፉ እውነተኛ  ታሪካችን እንድናውቅ የሚያደርግ ነው ብሏል ። ወጣቱ ትውልድ የአገሩን ታሪክ ለማወቅ ባህልና  ቋንቋ  ለማወቅ  የማንበብ  ባህሉን  እንዲያጎለብት ምክር ለግሷል ።
 
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም