በሩብ አመቱ ከወጪ ንግድ 723 ሚሊዮን ዶላር ገቢ ተገኘ

89
ህዳር 5/2012 የውጭ ንግድ ኮንትራክት አስተዳደር መመሪያ ተዘጋጅቶ ወደ ስራ በመገባቱ  በመጀመሪያው ሩብ  አመት የወጪ ንግድ ገቢ መጨመሩን የንግድና ኢንዱስትሪ ሚኒስቴር ገልጿል፡፡ በተያዘው በጀት አመት የመጀመሪያው ሶስት ወራትም  ከወጪ ንግድ 723 ሚሊዮን የአሜሪካ ዶላር  መገኘቱን ነው በሚኒስቴሩ የኮሙዩኒኬሽን ዳይሬክተር አቶ ወንድሙ ፍላቴ  የተናገሩት፡፡ ገቢው ከማዕድንና ከግብርና ምርቶች የተገኘ መሆኑንና ከባለፈው አመት ተመሳሳይ ወቅት ጋር ሲነጻጸርም  በ95 ሚሊዮን ዶላር ብላጫ  ያለው መሆኑን ነው የተገለጸው፡፡ የተሻለ ገቢ የተገኘው ለወጪ ንግድ እንቅፋት የነበረውን ኮንትራት የማፍረስ ችግርን የሚቀርፍ የውጭ ንግድ ኮንትራክት አስተዳደር መመሪያ ተዘጋጅቶ ወደ ሥራ በመገባቱ  እንደሆነም ነው  አቶ ወንድሙ የጠቀሱት፡፡ የውጭ ምንዛሬ ላይ እንቅፋት እየፈጠረ የነበረውን ችግር ለመቅረፍም፤ ነጋዴዎች በኮንትራታቸው ውል መሰረት ምርቱን እንዲያቀረቡና ኮንትራታቸውን እንዳያፈርሱ የሚያስችል መመሪያ በዚህ በጀት አመት መተግበር መጀመሩንም ተናግረዋል፡፡ መስኩ ውጤታማ ለእንዲሆን መመሪያውን የሚያስፈጽም ዳይሬክቶሬት ተቋቁሞ ወደ ስራ በመገባቱ ባለሃብቶች በኮንትራታቸው መሰረት እንዲሰሩ ድጋፍና ክትትል በማድረግ ውጤቱ መመዝገብ መቻሉን ነው ዳይሬክተሩ የገለጹት፡፡ ከዚህ በፊት ላኪዎች  ወደ ውጭ የሚላክ ምርትን በኮንትራቱ መሰረት ና ደረጃውን የጠበቀ ምርት በወቅቱ አለመላክ ለኮንትራት መፍረስ ምክንያት በመሆኑ የወጪ ንግዱን  ሲጎዳው  እንደቆየም ጠቅሰዋል፡፡ በመጀመሪያው ሩብ አመት የተገኘው የውጭ ምንዛሬ ገቢ ያደገ ቢሆንም በቂ አለመሆኑን የተናገሩት አቶ ወንድሙ፤ የኮንትሮባንድ ንግድ በተለይ ኢትዮጵያ ከፍተኛ ገቢ በምታገኝበት ቡና ና የቁም እንስሳት ምርት ላይ አሁንም ከፍተኛ ተጽዕኖ እያሳደረ ነው ብለዋል፡፡ በተያዘው በጀት አመት ኢትዮጵ ከማዕድን፣ ከግብርና እና ከኢንዱስትሪ ምርቶች የወጪ ንግድ  3 ነጥብ 73 ቢሊዮን የአሜሪካ ዶላር  ለማግኘት መታቀዱ ከሚኒስቴሩ ያገኘነው መረጃ ያመለክታል፡፡  
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም