የፖለቲካም ሆነ የታሪክ ቅራኔዎች የማንንም ህይወት ሳይቀጥፉ በውይይት መፈታት አለባቸው-ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ

85

አዲስ አበባ ኢዜአ ህዳር 4/2012 የፖለቲካም ሆነ የታሪክ ቅራኔዎች የማንንም ህይወት ሳይቀጥፉ በውይይት መፈታት እንዳለባቸው ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ አሳሰቡ።

ጠቅላይ ሚኒስትሩ ይህን ያሉት በኦሮሚያና አማራ ክልሎች የሚንቀሳቀሱ ተፎካካሪ የፖለቲካ ፓርቲዎች ዛሬ ውይይት ባደረጉበት ወቅት ነው።

ውይይቱ በሠላምና ጸጥታ ጉዳዮች ፣ የሁለቱ ክልሎች ህዝቦችና አንድነትን ማጠናከር እና ከሌሎችም የአገሪቱ ብሔር ብሔረሰቦች ጋር በመሆን የኢትዮጵያን አንድነት መጠበቅ ላይ ትኩረቱን አድርጓል።

በውይይቱ ከተፎካካሪ ፓርቲዎች በተጨማሪ የሁለቱ ክልሎች ከፍተኛ አመራሮችም ታድመዋል።

ጠቅላይ ሚኒስትሩ በዚህን ወቅት እንዳሉት፤ የፖለቲካ መጫዎቻ ህግን በትክክል ባለመገንዘብ አንዳንድ አካላት ለዜጎች ሞትና ንብረት መውደም ምክንያት እየሆኑ ነው።

አንደኛው የሌላኛውን ቁስል አለመገንዘቡ ደግሞ ችግሩን ይበልጥ እያባባሰው ይገኛል ነው ያሉት።

በመሆኑም አማራ ክልል የሚንቀሳቀሱ ፓርቲዎች ኦሮሚያ ያለውን ብሶትና ቅራኔ፤ በተመሳሳይ ኦሮሚያ ክልል የሚንቀሳቀሱት በአማራ ክልል ያለውን ቦታው ድረስ በመሄድ መገንዘብ እንዳለባቸው መክረዋል።

የአማራና ኦሮሞ ህዝቦች አብሮነት ታክቲካል ሳይሆን ዛሬም ነገም የሚቀጥል ነው ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ ፤ የፖለቲካም ሆነ የታሪክ ቅራኔ ካለ የሰው ህይወት ሳይጠፋ በንግግር እንዲፈታ አሳስበዋል።

የውይይት መድረኩ ይህን እውን ለማድረግ መዘጋጀቱን በመጠቆም።

በጠቅላይ ሚኒስትር ጽህፈት ቤት ፕሬስ ሴክሪታሪያት ሃላፊው አቶ ንጉሱ ጥላሁን በበኩላቸው በሁለቱ ክልሎች ውስጥ ቁጥራቸው በርካታ የአማራና ኦሮሞ ህዝቦች በጋራ እንደሚኖሩ አስታውሰዋል።

አሁን ያጋጠሙው ጊዜያዊ የጸጥታ ችግር ረዥም ዘመን የተሻገረውን የሁለቱን ህዝቦች አብሮነት እንደማይሸረሽረው  ጠቁመዋል።

ሁለቱ ህዝቦች በአብሮነት እንዲኖሩ ደግሞ ህዝቦቹን እንወክላለን የሚሉ ፓርቲዎች የሚጠበቅባቸውን ሚና መወጣት እንዳለባቸው በመግለጽ።

በሁለቱ ክልሎች ከሚንቀሳቀሱ የፖለቲካ ፓርቲዎች ውይይት ቀደም በሎ በሁለቱ ክልል የሚኖሩ ባላሃብቶች በአዲስ አበባ ዛሬ መምከራቸው ይታወሳል።

   
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም