ነዋሪዎቹ ሰላማቸውን በማስጠበቅ ልማታቸውን ለማፋጠን እንተጋለን አሉ

49
ዲላ ኅዳር 4 ቀን 2012 በደቡብ ኢትዮጵያ የገላናና አማሮ ወረዳዎች ነዋሪዎች ሰላማቸውን በማስጠበቅ ልማታቸውን ለማፋጠን እንደሚተጉ አረጋገጡ። በወረዳዎቹ አዋሳኝ 16 ቀበሌዎች የሰላም ግብረ ሃይሎች ተቋቁመው በጋራ  መንቀሳቀስ ጀምረዋል። ነዋሪዎቹ ሰላምን የሚያውኩ አካላትን ለሕግ አሳልፎ በመስጠት ዘላቂ ሰላም ለማረጋገጥ እንደሚሰሩም አስታውቀዋል። በምዕራብ ጉጂ ዞን የገላና ወረዳ የኤርጌሳ ቀበሌ ነዋሪው አቶ ጋዶ ቡሎ በአካባቢው በሚኖሩ ብሔሮች መካከል በሚከሰቱ ግጭቶች በማስቆም ሰላምን  ለማረጋገጥ ተዘጋጅቼያለሁ ብለዋል። መንግሥት ከአባ ገዳዎችና ከአገር ሽማግሌዎች ጋር በመሆን ግጭቶችን በባህላዊ እርቅ ለመፍታትና አንጻራዊ ሰላም ለማረጋገጥ  የጀመረውን ጥረት እንደሚያግዙ አረጋግጠዋል። የአማሮ ወረዳ ጃሎ ቀበሌ ነዋው አቶ ማረቆ ኡርጎ በበኩላቸው በአካባቢው ባለፉት ዓመታት በነበረው ግጭት ተፈናቅለው  እንደነበር አውስተው፣ሆኖም በተፈጠረው ሁኔታ ወደ ቀድሞ መኖሪያቸው በመመለሳቸው ዘላቂ ሰላምን በማረጋገጥ ድርሻዬን እወጣለሁ ብለዋል። የአማሮ ወረዳ ዋና አስተዳዳሪ አቶ ተፈራ ቦዶራ በበኩላቸው የጸጥታ አካሉ አካባቢውን ወደ ቀደሞ ሰላሙ ለመመለስ እየሰራ መሆኑን አመልክተዋል። በአጎራባች ወረዳዎች መካከል ያለውን የሕዝብ ለሕዝብ ግንኙነት ለማጠናከር ትኩረት መሰጠቱንም ገልጸዋል። በጃሎና ዳርባዬ በሚባሉ ቀበሌዎች የወደሙ ቤቶችን በመጠገን ከ21 ሺህ በላይ ተፈናቃዮችን ወደ ቀያቸው ለመመለስ እየተሰራ መሆኑን ዋና አስተዳዳሪው ተናግረዋል። የገላና ወረዳ ዋና አስተዳዳሪ አቶ ጃርሶ ዱጎ በበኩላቸው አካባቢውን ከጸጥታ ስጋት ነጻ ለማድረግ በየደረጃው ያለው የጸጥታ ሃይል ከኅብረተሰቡ ጋር በቅርበት እየሰራ መሆኑን ገልጸዋል። የምዕራብ ጉጂ ዞን ዋና አስተዳዳሪ አቶ አበራ ቡኖ በበኩላቸው በዞኑ ዘላቂ ሰላም  ለማስፈን ጥረት በመደረግ ላይ እንደሚገኝ አስታውቀዋል። ለዚህም ሕዝቡን በማንቀሳቀስና በማሳተፍ አጥፊዎች ሲያጋጥሙም ተከታትሎ ለሕግ እንደሚቀርቡ አስታውቀዋል። የአካባቢውን ሰላም በዘላቂነት ለማስጠበቅ በአዋሳኝ 16 ቀበሌዎች ኅብረተሰቡን ያሳተፈ የሰላም ግብረ ሃይል መቋቋሙ ተመልከቷል።
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም