በምእራብ ሸዋ ዞን 146 ኪሎ ሜትር መንገድ ተገንብቶ አገልግሎት መስጠት ጀመረ

55
አምቦ ሰኔ 13/2010 በምእራብ ሸዋ ዞን በዚህ አመት በመንግስትና በህብረተሰቡ ትብብር ከ152 ሚሊዮን ብር በሚበልጥ ወጪ ግንባታቸው ከተጀመሩ የመንገድ ፕሮጀክቶች ውስጥ  146 ኪሎ ሜትሩ ተጠናቆ ለትራፊክ ክፍት ሆነ። የዞኑ መንገዶች ባለስልጣን ጽህፈት ቤት ምክትል ኃላፊ አቶ ቀነኒሳ አብዲሳ እንዳስታወቁት በዚህ አመት ለአገልግሎት የበቃው መንገድ በበጀት ዓመቱ በገጠር መንገድ ተደራሽ መርሀግብር  ከተጀመረው 234 ኪሎ ሜትር ውስጥ ነው። በዞኑ የተለያዩ ወረዳዎች ተጠናቆ ለአገልግሎት በበቃው መንገድ ከግማሽ ሚሊዮን በላይ ህዝብ ተጠቃሚ ሆኗል። ከአዲስ መንገድ ግንባታም ሌላም የ200 ኪሎ ሜትር መንገድ ጥገና ስራም መከናወኑን ነው ምክትል ኃላፊው የገለጹት ፡፡ የቀሪው 80 ኪሎ ሜትር መንገድ ስራ 80 በመቶ መከናወኑና ወደ ሚቀጥለው በጀት ዓመት መተላለፉን ተናግረዋል። ከዚህም በተጨማሪ የ12 ድልድዮች ስራም ወደ ሚቀጥለው በጀት ዓመት የተላለፈ መሆኑን ጠቁመዋል፡፡ እንደ አቶ ቀነኒሳ ገለፃ ድልድዮቹ እያንዳንዳቸው 12 ሜትር ርዝመት አላቸው። በልማቱ ከመንገድ ስራ ተቋራጮች በተጨማሪ በሰባት ማህበራት የተደራጁ ከ2 ሺህ በላይ ወጣቶች በመሳተፍ 6 ነጥብ 5 ሚሊዮን ብር ገቢ በማግኘት ተጠቃሚ ሆነዋል። ለአገልግሎት የበቃውና ግንባታው በሂደት ላይ የሚገኘው መንገድ ሲጠናቀቅም 90 የገጠር ቀበሌዎችን እርስ በእርስና ከወረዳ ከተሞች ጋር ያገናኛል ተብሎ የሚጠበቅ ነው ። በዞኑ የጀልዱ ወረዳ አርሶ አደር ሌንጂሳ ኩማ በሰጡት አስተያየት ቀደም ሲል በመንገድ ችግር ምርታቸውን ለገበያ ማቅረብ ባለመቻላቸው ባገኙት ዋጋ ለመሸጥ ይገደዱ ነበር። ዘንድሮ ግን ክረምት ከበጋ አገልግሎት የሚሰጥ መንገድ ተገንብቶ ስራ በመጀመሩ የነበረባቸው ችግር መቃለሉን ገልጸዋል፡፡ የዳኖወረዳ አርሶ አደር አበበ ተፈራ በሰጡት አስተያየት ቀደም ሲል በአካባቢያቸው መንገድ ባለመኖሩ ምክንያት ምርታቸውን ለአካባቢ ገበያ ብቻ በማቅረብ  የልፋታቸውን ያህል ጥቅም ሳያገኙ መቆየታቸውን ገልፀዋል፡፡ በዚህ አመት ግን ቀበሌያቸውን ከሌሎች ቀበሌዎችና ከዋና መንገድ ጋር የሚያገናኝና ክረምት ከበጋ አገልግሎት የሚሰጥ መንገድ ተሰርቶ ለአገልግሎት በመብቃቱ መደሰታቸውን ተናግረዋል ። ምርታቸውን አጓጉዘውና ገበያ አማርጠው በተሻለ ዋጋ በመሸጥ ኢኮኖሚያዊ ተጠቃሚነታቸውን ለማሳደግ  እንደረዳቸው ተናግረዋል፡፡ የሊበን ጃዊ ወረዳ አርሶ አደር ዋቆ ፊጤ በበኩላቸው ቀደም ሲል በአካባቢያቸው መንገድ ባለመኖሩ ከፍተኛ ህክምና ለማግኘት የሚያደርጉትን ጉዞ አስቸጋሪና አድካሚ አድርጎት መቆየቱን አስታውሰዋል፡፡ የመንገዱ መሠራት የትራንስፖርት አገልግሎት ተጠቃሚ በመሆን ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ እንቅስቃሴያቸውን በማፋጠን ተጠቃሚ እንዳደረጋቸው ተናግረዋል፡፡ በተጨማሪም የምርት ማሳደጊያ ግብዓት ወደ አካባቢያቸው ለማጓጓዝና ምርታቸውንም ገበያ አውጥተው በተሻለ ዋጋ ለመሸጥ ምቹ ሁኔታ እንደፈጠረላቸው ገልፀዋል ።
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም