የኤርትራ ፕሬዝዳንት ኢሳያስ አፈወርቂ ኢትዮጵያ ላቀረበችው የሰላም ጥሪ የሰጡት ምላሽ ሁለቱን አገራት የሚጠቅም ነው- ዶክተር አብይ አህመድ

155
ወልቂጤ ሰኔ 13/2010 የኤርትራ ፕሬዝዳንት ኢሳያስ አፈወርቂ ኢትዮጵያ ላቀረበችው የሰላም ጥሪ የሰጡት ምላሽ ሁለቱን አገራት የሚጠቅም ነው ሲሉ የኢፌዴሪ ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ ገለጹ። ጠቅላይ ሚኒስትሩ ዛሬ በወልቂጤ ከተማዋና አካባቢው ማህበረሰብ ክፍሎች ውይይት ከማድረጋቸው ጎን ለጎን በአገራዊና ቀጠናዊ ጉዳዮች ላይ መግለጫ ሰጥተዋል። ዶክተር አብይ እንደገለጹት የኤርትራ ፕሬዝዳንት ኢሳያስ አፈወርቂ በአገሪቷ የሰማዕታት ቀን አከባበራቸው እለት ያሳዩት በጎ ምላሽ ለሁለቱ አገራት የሚጠቅምና የሚደነቅ ነው። ፕሬዝዳንቱ ለሰላም ጥሪው ለሰጡት መልካም ምላሽ ጠቅላይ ሚኒስትሩ ምስጋናቸውን አቅርበው፤ ኤርትራውያን ለነጻነታቸው የተዋደቁበት ቀን ለሁለቱ አገራት የጋራ በዓላችን ይሆናልም ብለዋል። አያይዘውም የደቡብ ሱዳን ፕሬዝዳንት ሳልቫኪር ማርዲያትና የተቃዋሚ ፓርቲ መሪ ዶክተር ሬክ ማቻር በአዲስ አበባ ከሚያደርጉት ውይይት የተሻለ ውጤት ይገኛል ብለው እንደሚገምቱ ገልጸዋል። ጠቅላይ ሚኒስትሩ አክለውም መጪው ጊዜ ለምስራቅ አፍሪካ ቀጠና አብሮነትና መከባበር ከፍ ያለ ደረጃ እንደሚመጣ ያለቸውን ተስፋ አውስተው ለዚህም ጠንክረን እንሰራለን ብለዋል። ፕሬዝዳንት ኢሳይያስ አፈወርቂ ከኢትዮጵያ ጋር “ገንቢ ውይይት” ለመጀመር ወደ አዲስ አበባ ልዑካን ቡድን እንደሚልኩ ዛሬ ጠዋት በኤርትራ ቴሌቪዥን ቀርበው እንዳሳወቁ በኬንያ የኤርትራ አምባሳደር በየነ ርዕሶም ለቢቢሲ መግለጻቸው የሚታወስ ነው። በጃፓን የኤርትራ አምባሳደር እስጢፋኖስ አፈወርቂም በይፋዊ የትዊተር ገጻቸው ይህንኑ አረጋግጠዋል።
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም