ሁለቱ ጎል ጠባቂ ዛፎች ግርምትን ፈጥረዋል

75
ህዳር 3/2012 አዲስ የተመረቀው በኮሎምቢያ ቦጎታ የሚገኘው አነስተኛ ሰው ሰራሽ ሜዳ ሁለት የማይንቀሳቀሱ ቋሚ ጎል ጠባቂ/በረኛ ዛፎችን አካቶ መገንባቱን ተከትሎ በርካቶችን አጀብ እያሰኘ መሆኑን ተነገረ ። በ2017 እ.ኤ.አ የመዝናኛ እና እስፖርት ዲስትሪክት ኢንስቲትዩት(IDRD) በዋና ከተማዋ ቦጎታ ሰሜናዊ ክፍል የሚገኘውን ፓርኩዌ ጃፖን የተሰኘውን መናፈሻ ለመለወጥና ለማሻሻል የምህንድስና እና ስነ ህንፃ ጥናት አደረገ። ተቋሙ በመናፈሻው ውስጥ ያሉ የተወሰኑ ዛፎችን በማስወገድ ወይም በማዛወር ሰው ሰራሽ የእግር ኳስና ቅርጫት ኳስ ሜዳ ለመስራት  ባቀደው መሰረት ማህበረሰቡን በማሳወቅ ስራዎችን እያከናወነ ቆይቷል። በአካባቢ ጥበቃ ረገድ ጠንካራ አቋም ያላቸው የቦጎታ ነዋሪዎች ዛፎቹን ከሜዳው የማስወገድ ዕቅድ የነበረውን የስራ ተቋራጭ ፍርድ ቤት ከሰው ረተውታል። ሆኖም ክሱ ይህን ስራ የሚያከናውኑ የግንባታ ባለሙያዎች የእግር ኳስ ሜዳውን ከመስራት ሊያግዳቸው እንዳልቻለ በዘገባው ተመልክቷል። በሜዳው ሁለት ጎሎች ትይዩ ቆመው ህይወታቸውን የቀጠሉት ዛፎች የሃገሪቱ ህግን ተገን በማድረግ ማንም ሊቀይራቸው የማይችል ቋሚ በረኞች ሆነው እስከ ዕድሜ ዘመናቸው አገልግሎት እንደሚሰጡ ኦዲቲ ሴንትራል አስነብቧል። ያልተጠበቁ ግብ ጠባቂዎቹ ዛፎች አንደኛው 4 ሜትር ከፍታ ያለው የዘንባባ ዛፍ ሲሆን ሌላኛው ደግሞ በበርካታ ቅርንጫፎች የታጀበ አጠር ያለ የዛፍ አይነት እንደሆነ ኦዲቲ ሴንትራል አስነብቧል። እንደ ዘገባው የማይንቀሳቀሱት የዛፍ ግብ ጠባቂዎች ከአንዳንድ ከሚንቀሳቀሱ በረኞች የተሻሉ እንደሆኑ በመግለፅ በተለያዩ የማህበራዊ መገናኛ ብዙሃን እየተጋሩ እንደሆነም ዘገባው አመልክቷል። (ኦዲቲ ሴንትራል)
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም