የጀርመኑ ሩቲንግ ንግድና ዘርፍ ማህበራት ምክርቤት ድጋፍ ሊያደርግ ነው

70
ህዳር 3/2012የጀርመኑ "ሩቲንግ" ንግድና ዘርፍ ማህበራት ምክርቤት ለአማራ ክልል ንግድና ዘርፍ ማህበራት ምክር ቤት ለአቅም ግንባታ ስራዎች የሚውል የ500 ሺህ ዩሮ የትብብር ድጋፍ ለማድረግ ተስማማ። የሁለቱ አቻ ምክር ቤቶች አመራሮችና ባለድርሻ አካላት በተገኙበት በባህር ዳር ከተማ ዛሬ ስምምነቱን ተፈራርመዋል። የአማራ ክልል ንግድና ዘርፍ ማህበራት ምክር ቤት ፕሬዚዳንት ኢንጅነር መላኩ እዘዘው በስምምነቱ ላይ እንደገለጹት ምክር ቤቱ 180 ከክልል እስከ ወረዳ የሚገኙ የንግድና ዘርፍ ማህበራት ምክር ቤቶችን በአባልነት አቅፎ የያዘ ነው። የንግድ ምክር ቤቱ የግሉን ክፍለ ኢኮኖሚ በማጎልበት የክልሉንም ሆነ የአገሪቱን ኢኮኖሚ በማፋጠን በኩል የበኩሉን ድርሻ እየተወጣ የሚገኝ መሆኑን ገልጸዋል። በዚህም ከጀርመኑ "ሩቲንግ" ንግድና ዘርፍ ማህበራት ምክር ቤት የተገኘው የ500 ሺህ ዩሮ የገንዘብ ድጋፍ የጀመረውን በጎ ተግባር አጠናክሮ ለማስቀጠልና የሚስተዋሉበትን ችግሮች ለመቅረፍ ያስችላል ብለዋል። በሦስት ዓመታት ውስጥ ለአቅም ግንባታና ለሌሎች ተያያዥ ስራዎች ማስፈፀሚያ የሚውለው የገንዘብ ድጋፍ የንግዱን ማህበረሰብ ለማሰልጠንና ለአባላቱ የአገር ውስጥና የውጭ ገበያ ለማፈላለግ የሚውል ይሆናል ተብሏል። በመንግስትና በንግዱ ማህበረሰብ መካከል የሚፈጠሩ ችግሮችን ለመፍታት የሚያስችሉ የምክክር መድረኮችን ለማመቻቸት ጭምር እንደሚጠቀሙበትም አስረድተዋል ። በተጨማሪም በንግዱ አለም ከፍተኛ ልምድ ባላቸውን የአገር ውስጥና የውጪ ሀገር ባለሙያዎች አማካኝነት ጥናትና ምርምር በማካሄድ በዘርፉ የሚስተዋሉ ችግሮችን ለመፍታት ገንዘቡ ጠቀሜታው የጎላ እንደሚሆን ተናግረዋል ። የጀርመኑ ሩቲግን የንግድና ዘርፍ ማህበራት የትብብር ስምምነት በአባል ምከር ቤቶች እስከ ታች ድረስ የሚስተዋሉ የእውቀትና የክህሎት ችግሮችን ለመቅረፍ ያግዛል ። የሩቲግን ንግድና ዘርፍ ማህበራት ምክር ቤት ዋና ዳይተሬክተር ሚስተር ማርቲን ፋህሊንግ በበኩላቸው እርሳቸው የሚመሩት የንግድና ዘርፍ ማህበራት ምክር ቤት በመንግስት በጀት ድጋፍ የሚደረግለት ነው። ከ170 ዓመት በላይ የካበተ ልምድ ያለው ምክር ቤቱ በንግዱ አለም የሚያጋጥሙ ችገሮችን ለመፍታት እውቀትና ክህሎት ያላቸው በርካታ ባለሙያዎችን ለማፍራት የበቃ መሆኑንም ገልጸዋል። በዚህም ያካበተውን ልምድና የከፍተኛ ባለሙያዎቹን አቅም በመጠቀም ከሰሃራ በታች ለሚገኙ ሀገራት የንግድና ዘርፍ ምክር ቤቶች የትብብር ድጋፍ በማድረግ ላይ እንደሚገኝ አብራርተዋል ። ከኢትዮጵያም የአማራ ክልልን ንግድና ዘርፍ ማህበራት ምክር ቤት የመጀመሪያው የትብብር ድጋፉን ተጠቃሚ የሆነ ምክር ቤት መሆኑን ገልፀዋል። በትብብሩም የአማራ ክልል የዘርፉ ተወካዮች በጀርመን ሀገር ሄደው የአጭር ጊዜ ስልጠናና የልምድ ልውውጥ እንዲያገኙ እንዲሁም ባለሙያዎችን በመላክ የአቅም ማጎልበቻ ስልጠና እንደሚሰጥ ቃል ገብተዋል። ጀርመን የኢትዮጵያን ኢኮኖሚ ለማጠናከር ፍላጎት አላት ያሉት ሚስተር ፋህሊንግ ተመሳሳይ ድጋፍ በሌሎች የኢትዮጵያ አካባቢዎችም ተጠናክሮ የሚቀጥል ይሆናል ብለዋል። የአማራ ክልል ንግድና ዘረፍ ማህበራት ምክር ቤት በኢትዮጵያ ንግድና ዘርፍ ማህበራት ምክር ቤት አባል ከሆኑ 18 ማህበራት መካከል አንዱ መሆኑን መረጃዎች ያመላክታሉ።                  
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም