በጅማ ዩኒቨርሲቲ የመማር ማስተማር ስራው ሰላማዊ ሆኖ እንዲቀጥል እየተሰራ ነው

90
ጅማ (ኢዜአ) ህዳር 3 ቀን 2012 ዓ.ም በጅማ ዩኒቨርሲቲ የመማር ማስተማር ስራው የተረጋጋና ሰላማዊ ሆኖ እንዲቀጥል እየሰራ መሆኑን ዩኒቨርሲቲው አስታወቀ፡፡ የዩኒቨርሲቲው ማህበረሰብ አባላትና ከፍተኛ የሥራ ኃላፊዎች በወልዲያ ዩኒቨርሲቲ ሰሞኑን ተከስቶ በነበረው ግጭት ሕይወታቸውን ላጡና ጉዳት ለደረሰበቸው ተማሪዎች የተሰማውን ጥልቅ ሀዘን ገልጸዋል፡፡ በጅማ ዩኒቨርሲቲ የውጭ ግንኙትና ኮሚኒኬሽን ሲኒየር ዳይሬክተር ዶክተር አሸናፊ በላይ በተማሪዎቹ ላይ የደረሰው ጉዳት ተቀባይነት የሌለውና የጥፋት ተግባር በመሆኑ እንደሚያወግዙት ገልጸዋል። የሚመለከታቸው የመንግስት አካላት የችግሩን አሳሳቢነት ተገንዝበው በአስነዋሪ ድርጊት ውስጥ የተሳተፉ አካላት ላይ ህጋዊ እርምጃ እንዲወሰድ ጠይቀዋል፡፡ በዩኒቨርሲቲው በአሁኑ ወቅት ያለውን ሰላማዊ የመማር ማስተማር ሂደት አጠናክሮ ለማስቀጠል የተቋሙን ማህበረሰብ ያሳተፈ ሥራ እየተከናወነ መሆኑን ገልጸዋል። በመሆኑም የጅማ ዩኒቨርሲቲ ተማሪዎችም ከየትኛውም ጊዜ በላይ አንድነታቸውን በማጠናከርና በመረጋጋት የመማር ማስተማር ሥራው ሰላማዊ ሆኖ እንዲቀጥል የበኩላቸውን እንዲወጡ ጠይቀዋል። የጅማ ዩኒቨርሲቲ የተማሪዎች ሕብርት ፕሬዚዳንት ተማሪ አሚን መሃመዲ በበኩሉ በወልዲያ ዩኒቨርሲቲ ተፈጥሮ በነበረው ችግር በተቋማቸው የማማር ማስተማር ስራው መቋረጡን ተናግሯል፡፡ በእዚህም የደህንነት ስጋት ያደረባቸውን ተማሪዎች የኦሮሞ ብሔር ተወላጅ ተማሪዎች የማረጋገት ሥራ እያከናወኑ መሆናቸውን ጠቁመዋል፡፡ "አንዳንድ ተማሪዎች አሁንም በስጋት ምክንያት በሃይማኖት ተቋማት ውስጥ ተጠልለው ይገኛሉ" ያለው ፕሬዚዳንቱ፣ ዩኒቨርሲቲውን ለቀው ወደቤተሰቦቻቸው የተመለሱ መኖራቸውንም ጠቁሟል። ሥጋት የገባቸው ተማሪዎች እንዲረጋጉና ወደትምህርት ገበታቸው እንዲመለሱ የማድረግ ሥራ እየተሰራ መሆኑንም ተማሪ አሚን አስታውቋል፡፡ የጅማ ከተማ ነዋሪ አቶ ሸመሱ ኑረዲን በበኩላቸው በጅማ ከተማ ምንም አይነት ሥጋት እንደሌለና በርካታ ተማሪዎች በሰላም እየተንቀሳቀሱ መሆናቸውን ተናግረዋል። የከተማው ህዘብ ለተማሪዎች ያለው አመላካከት አዎንታዊ መሆኑን ገልጸው በዩኒቨርሲቲው ውስጥ የሚስተዋለው  አለመተማመን ተማሪዎች ተረጋግተው እንዳይማሩ እያደረገ መሆኑን ተናግረዋል። "ችግሩ እንዲስተካከል ለተማሪዎች ጥሩ አቅባበል ከማድረግ ባለፈ የዩኒቨርሲቲው አመራር በተማሪዎች አንድነት ላይ ጠንክሮ እንዲሰራ ጠይቀናል" ብለዋል፡፡    
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም