በሸርቆሌ ስደተኞች ካምፕ የወደመው ደን መተካት ተችሏል

62
አሶሳ ኢዜአ ህዳር 03 / 2012 ዓ.ም.፡- በቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል ከ20 ዓመታት በላይ በቆየው ሸርቆሌ ስደተኞች ካምፕ የወደመውን የተፈጥሮ ሃብት መልሶ መተካት መቻሉን የክልሉ ግብርናና ተፈጥሮ ሃብት ቢሮ ገለጸ፡፡ በ1990 ዓ.ም. አካባቢ የተቋቋመው በሆሞሻ ወረዳ የሸርቆሌ ስደተኞች ካምፕ ከተለያዩ የአፍሪካ ሃገራት የመጡ በ10 ሺህዎች የሚቆጠሩ ስደተኞች ከ20 ዓመታት በላይ ኖረውበታል፡፡ ስደተኞቹ በካምፑ አካባቢ የሚገኘው የተፈጥሮ ደን በህገ-ወጥ መንገድ ለማገዶ፣ ለመኖሪያ ቤት ግንባታ እና ሌሎችም ፍጆታዎች በማዋላቸው የተፈጥሮ ሃብቱ ጉዳት ደርሶበታል፡፡ በተለይ በሰባት ዓመት አንድ ጊዜ የሚያፈራውን የክልሉ ቆላ ቀርከሃን ጨምሮ በቀላሉ የማይተኩ የተፈጥሮ ደኖች መውደማቸውን የግብርናና ተፈጥሮ ሃብት ቢሮ ሃላፊ አቶ ሙሳ አህመድ ይናገራሉ፡፡ ቢሮው ህብረተሰቡን እና በተፈጥሮ ሃብት ክብካቤ ላይ የሚሠሩ ድርጅቶችን በማስተባበር ባለፉት ለረጅም ዓመታት የተፈጥሮ ሃብት ጥበቃና ክብካቤ ማከናወኑን አመልክተዋል፡፡ በዚህም የተራቆተውን የካምፑ አካባቢ መልሶ ማገገሙን ጠቁመው የወደመውም ደን መተካት እንደተቻለ አስረድተዋል፡፡ እርሳቸው እንደሚሉት የአካባቢውን ማህበረሰብ እና ስደተኞችን ከችግኝ ተከላ ጀምሮ በማሳተፍ ተጠቃሚ ለማድረግ ጥረት ተደርጓል፡፡ ከምንም በላይ የወደመውን የተፈጥሮ ሀብት መልሶ መተካት እንደሚቻል ክልሉ በተግባር ተሞክሮ የወሰደበት የአካባቢ ጥበቃ ሥራ እንደሆነ አቶ ሙሳ አብራርተዋል፡፡ የተገኘውን ውጤት ዘላቂ ለማድረግ የለማውን ደን ለአካባቢው ማህበረሰብ በባለቤትነት የማስተላለፍ ስራ ይጠብቀናል ብለዋል ፡፡ በተለይ ስደተኞችን በማስተማር ሃብቱን ከጥፋት መጠበቅ ሌላው ተግባር እንደሆነ አመልክተው በግዴለሽነት ሃብቱ ላይ ጥፋት የሚያስከትሉት ደግሞ በህግ እንደሚጠየቁ አስታውቀዋል፡፡ የመልሶ ማልማት ፕሮጀክቱ አስተባባሪ አቶ ጌታቸው ጥላሁን እንደሚሉት በካምፑና አካባቢው የወደመውን ደን  መልሶ ለመተካት 18 ዓመታት ጠይቋል ። የአካባቢ ጥበቃ ሥራው ኢኮኖሚያዊ ጠቀሜታ ያላቸውን ማንጎ፣ ዕጣንና ሙጫ ተክሎችን ጨምሮ ሌሎችንም ኢኮኖሚያዊ ጠቀሜታ ያላቸው የዛፍ ዝርያዎች ያካተተ ነው ብለዋል፡፡ በካምፑ አካባቢ የተራቆተ ከ620 ሄክታር በላይ መሬት መልሶ ማልማት እንደተቻለ ገልጸዋል፡፡ በወረዳው የወምባ ቀበሌ ነዋሪ አቶ አሊ ሙሳ በስደተኞች ካምፕ አካባቢ የወደመውን የተፈጥሮ ሃብት ለመመለስ በተከናወነ የተፋሰስ፣ እርክንና ችግኝ ተከላ ሥራ የተገኘው ውጤት የሚበረታታ እንደሆነ ይናገራሉ፡፡ ይሁንና ከቀበሌ መስተዳደር ጀምሮ ህብረተሰቡን በማስተባበር መልሶ የለማው ደን ለመጠበቅ የተደረገው ጥረት አነስተኛ በመሆኑ ተጨማሪ ውድመት እየደረሰበት ነው ብለዋል፡፡ በግላቸው ችግሩን በመከላክል አካባቢውን በዘላቂነት አረንጓዴ ለማድረግ የተጀመረው ውጤት ግቡን እንዲመታ ጠንክረው እንደሚሰሩ ገልፀዋል ። በሸርቆሌ ስደተኞች ካምፕ ተወልዶ ያደገው ሱዳናዊው ወጣት ነስረዲን አደም በበኩሉ ስደተኞች የአካባቢውን ተፈጥሮ ደን በመጠቀማቸው አካባቢው እንደተራቆተ ተናግሯል፡፡ ለረጅም ዓመታት በካምፑ የተከናወነው የተፈጥሮ ሃብት ጥበቃ ሥራ የአካባቢውን አየር በመቀየር ለስደተኞች ኑሮ ምቹ እያደረገው መምጣቱን ገልጿል፡፡        
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም