ውህደቱ በመከባበር ላይ የተመሰረተች ህብረ ብሄራዊት ኢትዮጵያን ለመገንባት እንደሚያስችል የምክር ቤት አባላት ገለጹ

70
ባህርዳር ህዳር  3/2012 በመደመር እሳቤ የሚካሄደው የኢህአዴግ አባል እና አጋር ድርጅቶች ውህደት በመከባበር ላይ የተመሰረተች ጠንካራ ህብረ ብሄራዊት ኢትዮጵያን ለመገንባት እንደሚያስችል የአማራ ክልል ምክር ቤት አባላት ተናገሩ። አባላቱ ለኢዜአ እንዳሉት በዘር ላይ የተመሰረተው ፖለቲካ ለዘመናት የተገነባነውን የአብሮነት እሴት በመሸርሸር ሀገሪቱን ወደ አልተፈለገ የእርስ በእርስ ግጭት ያስገባ አዋጭ ያልሆነ አካሄድ ነው። ከአባላቱም መካከል አቶ ወርቁ አዳሙ በሰጡት አስተያየት " የፓርቲዎቹ ውህደት የፌዴራል ስርዓታችንን በማጠናከርና ብዝሃነታችንን አስጠብቀን የሀገራችን አንድነት እንድንቀጥል የሚያስችል ነው" ብለዋል። እንደሚካሄድ የሚጠበቅ የፓርቲዎች ውህደት እስካሁን በተጓዙበት ሂደት የተገኙ መልካም ተሞክሮዎችን በመወስድና ስህተቶችን በማረም ወጥነት ያለው ስርዓት ለመገንባትም እንዲሁ። "አንዳንድ ወገኖች እንደሚሉት የፌዴራል ስርዓቱንና ብዝሃነትን በመናድ ወደ አሃዳዊ ስርዓት ለመመለስ እየተሰራ ነው በሚል በመደመር እሳቤ የሚካሄደውን ውህደት የሚነቅፉት የግል ጥቅማቸውን የሚያስቀር ሆኖ ስላገኙት ብቻ ነው" ብለዋል። አስተያየት ሰጪው እንዳስረዱት ውህደቱ ማንነትን የሚጥስ ሳይሆን በአስተሳሰብ አንድ በመሆን በየአካባቢው አሁን የሚታዩ ግጭቶችን፣ ጽንፈኝነትንና አክራሪነትን በጋራ አመራር ታግሎ በማስተካከል ኢትዮጵያዊ አንድነትን ያጠናክራል። ብሔርን ምሽግ አድርገው እርስ በእርስ ግጭት እንዲፈጠር እየሰሩ ያሉ አካላት ውህደቱ የግል ጥቅማቸውን የሚያስቀር በመሆኑ እንዳይሳካ በየአካባቢው ግጭት በማስነሳት ችግር እየፈጠሩ እንደሚገኙ ተናግረዋል። "ችግሩን በዘላቂነት ለመፍታትም ብሔረሰብና ሀገራዊ ማንነትን በማዋሃድ አሁን የሚስተዋሉ ዋልታ ረገጥ አስተሳሰቦችን በማቀራረብ የፓርቲዎች ውህደትን ማፋጠን አማራጭ የለውም "ብለዋል። ሌላኛው የምክር ቤት አባል አቶ ዕውነቴ አለነ በበኩላቸው የኢትዮጵያን ህዝቦች በጋራ የሚመራቸው ወጥ የሆነ የፖለቲካ ፓርቲ ውህደት እስካሁን መዘግየት እንዳልነበረበት ተናግረዋል። እስካሁን የነበረው የኢህአዴግ የግንባር አደረጃጀትና ጉዞ አፋር፣ ሶማሌ፣ ቤንሻነጉልና ጋምቤላን በአጋር ድርጅትነት ስም ያገለለ ሆኖ መቆየቱ ተገቢ እንዳልሆነ። አቶ ዕውነቴ እንደገለጹት በመደመር እሳቤ የሚደረገው የፓርቲዎች ውህደት ሁሉንም ፓርቲዎች በእኩል ደረጃ በማሳተፍ በሀገራዊ ውሳኔና አተገባበር እንዲሁም አድሎና የፍትሃዊነት መጓደል የሚፈጠርበት ሁኔታ አይኖርም። እስካሁን በሀገር ላይ ጉዳት ሊያደርስ የሚችል ሀሳብ ሲመጣ ተገቢ አይደለም ብለህ ለመታገል ያስፈራ የነበረበት ጊዜ እንደነበር አውስተው ውህደቱ ይህን ችግር በመፍታት ሃሳቦችን ፊት ለፊት ተጋፍጦ ለማስተካከል ምቹ ሁኔታ እንደሚፈጥር አመልክተዋል። "አሁን ያለውን የፌዴራሊዝም ስርዓትም ይበልጥ እንዲያብብና ከልዩነት ይልቅ የጋራ እሴቶቻችንን በማጎልበት ቀጣይ ሀገር ተረካቢውን ትውልድ በአንድነት ላይ አተኩሮ ለመገንባት ያስችላል" ሲሉም ገልጸዋል። " ስንወሃድ ማንነት ሊደፈጥጥ ይችላል ብለን የምናስባቸውን ነጥቦች ለይተን ይዘን ካልተወሃድን የራሱ ችግር ሊኖረው ይችላል "ያሉት ደግሞ ሌላው የምክር ቤት አባል ወይዘሮ ወለላ መብራት ናቸው። ጭንቃቄ በማድረግ ብሔሮች ፣ ብሔረሰቦችና ህዝቦች የራሳቸውን ማንነት እንደያዙ ውህደቱ የሚፈፀም ከሆነ የጠነከረችና የበለፀገች ኢትዮጵያን መገንባት እንደሚቻል ተናግረዋል። "ማንነቱ የተከበረና የተደመጠ ህዝብ ሉአላዊነቷ የተከበረ ሀገር ሊፈጥር ይችላል "ያሉት ወይዘሮ ወለላ የሚካሄደው ውህደትም በብሔርና በጎጥ የሚነሳውን ጥላቻና ቁርሾ በዘላቂነት ያስቀራል ብለው እንደሚያምኑ አስረድተዋል። አቶ ሙሉጌታ ደባሱ በበኩላቸው ለዘመናት የተገነባው የአንድነት እሴት መሸርሸር የጀመረው ሁሉም ወደየአካባቢው አጥቦ የመመልከት አስተሳሰብ እየተስፋፋ በመምጣቱ እንደሆነ ገልጸዋል። በማያያዝም እንዳሉት የብሔሮች ፣ ብሔረሰቦችና ህዝቦች ባህል፣ ቋንቋ፣ ዕምነትና እሴት ጠብቆ የሚካሄደው የፓርቲዎች ውህደትም በመከባበር ላይ የተመሰረተ ኢትዮጵያዊ አንድነትን ለማምጣት በጎ አስተዋፅኦ ይኖረዋል። ውህደቱ አንድ ወገን ብቻ የዚህችን ሀገር ችግር የምፈታው እኔ ብቻ ነኝ የሚለው አስተሳሰብ በማስቀረትና አግላይነትን በማስወገድ ሁሉም እኩል የሚሳተፍበትና የሚወስንበትን ዕድል እንደሚፈጥር አስተያተ ሰጪዎቹ አብራርተዋል።    
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም