የሰሜን ተራሮች ብሄራዊ ፓርክን የሚጎበኙ የውጪ ሀገር ቱሪስቶች ቁጥር እየጨመረ ነው

128
ህዳር 3/2012 የሰሜን ተራራች ብሄራዊ ፓርክን የሚጎበኙ የውጪ ሀገር ቱሪስቶች ቁጥር ካለፉት ዓመታት በተሻለ እየጨመረ መምጣቱን የፓርኩ ጽህፈት ቤት አስታወቀ፡፡ በፓርኩ ጽህፈት ቤት የህብረተሰብና ቱሪዝም ኃላፊ አቶ ታደሰ ይግዛው ለኢዜአ እንደተናገሩት በሀገሪቱ አንዳንድ አካባቢዎች አልፎ አልፎ አለመረጋጋት ቢከሰትም ፓርኩን የሚጎበኙ የውጪ ሀገር ቱሪስቶች ቁጥር  እየጨመረ መጥቷል። በተያዘው የበጀት ዓመት የመጀመሪያዎቹ ሶስት ወራት ብቻ ፓርኩን ከጎበኙ ከሰባት ሺህ በላይ የውጭ ሀገራት ቱሪስቶች ሰባት ሚሊዮን 500 ሺህ  ብር የአካባቢው ማህበረሰብና መንግስት ገቢ ማግኘታቸውን  ገልጸዋል። ከገቢ ውስጥም በኢኮ-ቱሪዝም ማህበራት የተደራጁ ከሰባት ሺህ በላይ የህብረተሰብ ክፍሎች ስድስት ሚሊዮን ብር የሚጠጋ ድርሻ እንደሆነ ጠቁመው ቀሪው ከመግቢያ ትኬትና ከፊልም ቀረጻ መንግስት ያገኘው መሆኑን አስረድተዋል። እንደ ኃላፊው ገለጻ ህብረተሰቡ ገቢውን ያገኘው ለቱሪሰቶች ምግብ በማብሰል፣ ዕቃ በመጫንና በማጓጓዝ፣ በማጀብ፣ መንገድ በመምራት፣ በቅሎ በማከራየትና በማስጎብኘት ከሰጠው አገልግሎት  ነው። ከቱሪዝም ገቢው ተጠቃሚ የሆኑት የፓርኩ አዋሳኝ በሆኑት ደባርቅ ከተማ ፣አዲአርቃይ ፣ጃናሞራ ጠለምትና በየዳ ወረዳዎች የሚገኙ ወጣቶች አርሶአደሮችና የስካውት አባላት ናቸው። ፓርኩን የጎበኙት ቱሪስቶች ቁጥር ከአምናው ተመሳሳይ ወቅት ጋር ሲነጻጸር በ3ሺ ጭማሪ እና ገቢውም እድገት ማሳየቱን ኃላፊው ጠቅሰዋል። ለቱሪስት ፍሰቱ መጨመርም ዓለም አቀፍ የቴክኖሎጂ አማራጮችን በመጠቀም ፓርኩንና በውስጡ ያሉ መስህቦችን  ጭምር ለማስተዋወቅ የተደረገው ጥረት ከፍተኛ አስተዋጽኦ እንደነበረው  ተመልክቷል። የደባርቅ ከተማ ነዋሪው ወጣት ሲሳይ መንግስቴ በሰጠው አስተያየት "ባለፉት ሶስት ወራት ለቱሪስቶች ምግብ በማብሰል ከ12ሺ ብር በላይ ገቢ በማግኘት ተጠቃሚ ሆኛለሁ " ብሏል። የወር ተራ ሲደርሰው ከግብርና ስራቸው በተጓዳኝ  ጓዝ በመጫንና በቅሎ በማከራየት በወር እስከ ሁለት ሺህ ብር ገቢ እንደሚያገኙ የገለጹት ደግሞ አርሶአደር ሞላልኝ መክብብ ናቸው፡፡ የፓርኩ አካባቢ ህብረተሰብ ከቱሪዝም ገቢው ተጠቃሚ እንዲሆን መደረጉ ለተፈጥሮ ሀብቱ ያለውን የባለቤትነትና የተቆርቋሪነት ስሜት እንዲጎለብት ምቹ ሁኔታ እየፈጠረ መሆኑን አመልክተዋል። የሰሜን ብሄራዊ ፓርክ 412 ስኩየር ኪሎ ሜትር ስፋት ያለው ሲሆን እንደ አውሮፓውያን የዘመን አቆጣጠር በ1978 በተባበሩት መንግስታት የትምህርት የሳይንስና የባህል ድርጅት / ዩኔስኮ/ በአለም ቅርስነት የተመዘገበ የተፈጥሮ ሀብት ነው።ፓርኩ በኢትዮጵያ ብቻ የሚገኙትን ዋልያ፣ ቀይ ቀበሮና ጭላዳ ዝንጀሮን ጨምሮ ሌሎች የብርቅዬ የዱር እንስሳትና አእዋፋት መገኛ ስፍራ መሆኑ ይታወቃል፡፡    
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም