መደመር በአገሪቷ ኢኮኖሚ ዕድገት ላይ ተጋርጦ የነበረውን አደጋ በመሰረታዊነት መፍታት የሚያስችሉ አቅጣጫዎችን አስቀምጧል - ምሁራን

73
ህዳር 3/2012 መደመር በኢትዮጵያ የኢኮኖሚ ዕድገት ላይ ተጋርጦ የነበረውን አደጋ በመሰረታዊነት መፍታት የሚያስችሉ የመፍትሔ አቅጣጫዎችን ያስቀመጠ እሳቤ መሆኑን የምጣኔ ሀብት ምሁራን ገለጹ። በጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ ሐሳብ አመንጪነት የመጣው ''መደመር'' አገሪቷ የነበራትን መጥፎ ታሪክ በመቀየርና ከነበሩ ወረቶች ተነስቶ የተሻለ በመስራት ወደ ብልጽግና የመሸጋገር እሳቤን ያዘለ ነው። እሳቤው በተለይም በአገሪቷ ባለፉት ዓመታት የተመዘገቡ ኢኮኖሚያዊ፣ ፖለቲካዊና የውጭ ግንኙነት ስራዎች አሁን ከተገኘው ውጤት የበለጠ መሆን ይችል ነበር የሚል እምነት አለው። አገሪቷ በታሪክ አጋጣሚ ያሳለፈቻቸው መጥፎ ክስተቶችን በማረምና ጠንካራ ጎኖችን በማጎልበት ወደ ብልጽግና መድረስ የሚቻል መሆኑንም እሳቤው አጽንኦት ሰጥቶታል። ለኢዜአ አስተያየታቸውን የሰጡ የምጣኔ ሃብት ምሁራን ''መደመር'' በአገሪቷ ኢኮኖሚ ዕድገት ላይ ተጋርጦ የነበረውን አደጋ በመሰረታዊነት መፍታት የሚያስችሉ አቅጣጫዎችን ያስቀመጠ እሳቤ መሆኑን ነው የገለጹት። የምጣኔ ሃብት ምሁሩ ዶክተር ተሾመ አዱኛ ''የመደመር ጽንሰ ሀሳብ የኢትዮጵያ ኢኮኖሚ ላይ መሰረታዊ ለውጥ ለማምጣት በወሳኝ ጊዜ የመጣ ነው'' ይላሉ። በኢትዮጵያ በተለይም ባለፉት ሁለት አስርተ ዓመታት በመሰረተ ልማት ረገድ የተመዘገበው ውጤት ከፍተኛ መሆኑን ጠቅሰው፤ ይህም አሁን ላይ መነሻ የሚሆንና ለቀጣይ የኢኮኖሚ ማሻሻያ ትልቅ ድጋፍ የሚያደረግ መሆኑን በእሳቤው በአግባቡ ተቀምጧል ብለዋል። የመደመር እሳቤ በተለይም በምጣኔ ሃብት ዘርፉ ያለፉትን ጥፋቶችና ጠንካራ ስራዎችን በመለየት በቀጣይ የተሻለ ስራ መስራት የሚያስችሉ አቅጣጫዎችን የሚያመላክት መሆኑንም አብራርተዋል። መደመር እስካሁን የተመዘገበው የኢኮኖሚ ዕድገት ፍትሃዊ ሃብት ማፍራትን መሰረት ቢያደርግና የግል ዘርፉን በስፋት ያሳተፈ ቢሆን ቀደም ሲል ከተመዘገበው የኢኮኖሚ ዕድገት የተሻለ ማስመዝገብ ይቻል እንደነበር ማመላከቱ ሁሉንም የሚያስማማ መሆኑንም አረጋግጠዋል። መደመር እስካሁን በአገሪቷ የመጡትን ለውጦች እንዲሁም ከለውጡ ጋር የመጡ ስህተቶችን በመቀበል ስህተቶችን ማስተካከል ላይ አጽንኦት የሚሰጥ መሆኑንም ዶክተር ተሾመ ያብራራሉ። ሌላው የምጣኔ ሃብት ባለሙያ አቶ ዘመዴነህ ንጋቱ በጠቅላይ ሚኒስትሩ የሚቀነቀነው የመደመር እሳቤ የአገሪቷን ኢኮኖሚ በአጭር ጊዜ ለማሻሻል የሚያስችሉ አቅጣጫዎችን ያመላከተ መሆኑን ተናግረዋል። ተወዳዳሪነትን በመጨመርና በመንግስት የተያዙ አገልግሎት ሰጪ ተቋማትን በከፊል ወደ ግል ዘርፉ በማዘዋወር የተጀመሩ ስራዎችም አገሪቷ በዘርፉ መሰረታዊ ለውጥ ለማምጣት ያላትን ፍላጎት የሚያሳይ መሆኑን በመጥቀስ። እንደ አቶ ዘመዴነህ ገለጻ፣ የመደመር እሳቤ "የመንግስትን ሚና ሳያሳንስ የግል ዘርፉን ተወዳዳሪነት የሚያሰፋና ወደ ጋራ ብልጽግና የሚያደርስ ነው"። መደመር  የሰው ልጆችን ድምር ፍላጎቶችን ተሳቢ ያደረገ፣ ከድጎማና ከሃብት ክፍፍል ይልቅ ምርታማነትን ማሳደግና የጋራ ብልጽግና ማምጣት ላይ ትኩረት ያደረገ አገራዊ ለውጡ የሚመራበት እሳቤ ነው።    
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም