በትግራይ እየተካሄደ ባለው የዋንጫና የብቃት መለኪያ ውድድር አክሱም ኃውልት ክለብ በ 6 ነጥብ እየመራ ነው

62
መቀሌ (ኢዜአ) ህዳር 03 ቀን 2012ዓ.ም --- የትግራይና ሁለት የደቡብ ክልል የእግር ኳስ ክለቦች በተሳተፉበትና በመካሄድ ላይ ባለው የዋንጫና የብቃት መለኪያ ውድድር አክሱም ኃውልት ክለብ በ 6 ነጥብ እየመራ ነው። አራተኛ ቀኑን በያዘው በዚህ ውድድር ላይ ሁለት የደቡብ ክልል ክለቦችን ጨምሮ በትግራይ ክልል የሚገኙ ስምንት የእግር ኳስ ክለቦች በመሳተፍ ላይ ናቸው። ክለቦቹ በሁለት ምድቦች ተከፍለው እስካሁን ባካሄዱት ግጥሚያ የአክሱም ኃውልት የእግር ኳስ ክለብ ስድስት ነጥቦችን በመሰብሰብ እየመራ ይገኛል። በትግራይ ክልል ወጣቶችና ስፖርት ጉዳይ ቢሮ የእግር ኳስ ፌደረሽን ጽህፈት ቤት ኃላፊ አቶ አንገሶም ካህሳይ እንዳሉት፣ ቡድኑ ከደደቢትና ከመቀሌ 70 እንደርታ ክለቦች ጋር ያደረጋቸውን ሁለት ግጥሚያዎች በአሸናፊነት በማጠናቀቁ እየመራ ነው። እስካሁን በሰበሰበው 6 ነጥብም ከምድቡ አንደኛ ደረጃ ይዞ ለቀጣይ ግማሽ ፍጻሜ ውድድር ማለፉን አረጋግጧል። የወላይታ ዲቻ እግር ኳስ ክለብ በ4 ነጥብ ሁለተኛ ደረጃን ይዞ እየተከተለ ይገኛል። የወላይታ ዲቻ እግር ኳስ ክለብ የሁለተኛ ደረጃን ይዞ እየተከተለ ያለው ደደቢትን 2 ለ 1 በሆነ ውጤት በማሸነፍና ከመቐለ 70 እንደርታ ጋር ደግሞ እኩል ዜሮ ለዜሮ በመለያየቱ ነው። የደደቢት እግር ኳስ ክለብ እስከ አሁን ባካሄዳቸው ሁለት ጨዋታዎች ምንም ነጥብ ሳይዝ ቀርቷል። እንደኃላፊው ገለጻ አጨዋወት ብቃት መቐለ 70 እንደርታና ወላይታዲቻ የእግር ኳስ ክለቦች የተሻሉ ሆነው ተገኝተዋል። ዛሬ አድዋ ሶሎዳ ክለብ ከሲዳማ ቡና ጋር ከቀኑ 9፡00 ሰዓት ላይ ተገናኝተው ግጥሚያቸውን እንደሚያካሂዱ ከወጣው የጨዋታው መርሃ ግብር ለማወቅ ተችሏል። ውድድሩን በሚካሄድበት የትግራይ ዓለም አቀፍ ስታዲዮም ተገኝተው አስተያየታቸው ከሰጡ የመቀሌ 70 እንደርታ ደጋፊዎች ማህበር አመራር መካከል አቶ ዮሐንስ ታደለ፣ ውድድሩ ሁለት ዓላማዎችን እያሳካ መሆኑን ገልጸዋል። ውድድሩ ለአሸናፊ ክለብ የዋንጫና የማበረታቻ የገንዘብ ሽልማት ከማስገኘት ባለፈ በክለቦች መካከል ፍቅርና አንድነትን ለማጠናከር የሚያግዝ ነው። "ክለቦቹ ብቃታቸውን በመለካት በቀጣይ የተሻለ ዝግጅት እንዲያደርጉ ያነሳሳል" ብለዋል የአክሱም ኃውልት እግር ኳስ ክለብ ሥራ አስፈፃሚ የሆኑት አቶ ክንፈ ወልደምህረት በበኩላቸው፣ "ከመቐለ 70 እንደርታ እና ከወላይታ ዲቻ ያገኘናቸው ልምዶች ክለባችንን ለዋንጫ ፉክክር ጠንካራ ተወዳዳሪ እንዲሆን የሚያደርግ  ነው" ብለዋል። ውድድሩ ክልልና አገር ወክለው የሚወዳደሩ ብቁ ስፖርተኞችን ለመመልመል የሚያግዝ መሆኑንም አቶ አንገሶም ገልጸዋል።    
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም