ሴቶችን በአደረጃጀት በማሳተፍ ተጠቃሚነታቸውን ለማረጋገጥ በትኩረት እየተሰራ ነው

204
ደብረ ማርቆስ ኢዜአ ህዳር 3 ቀን 2012 ዓ.ም ..... ሴቶችን በአደረጃጀት በማሳተፍ ዘላቂ ተጠቃሚነታቸውን ለማረጋገጥ ትኩረት ሰጥቶ እየሰራ መሆኑን የአማራ ክልል ሴቶችና ህፃናት ጉዳይ ቢሮ ገለፀ ። የሴት አደረጃጀቶችን በማህበራዊ፣ በኢኮኖሚያዊና በፖሊካዊ ጉዳዮች ያላቸውን ተሳትፎና ተጠቃሚነት ለመገምገም የሚያስችል ጉብኝት በምስራቅ ጎጃም ዞን ደብረኤሊያስ ወረዳ ለሁለት ቀናት ተካሔዷል። የአማራ ክልል ሴቶችና ህጻናት ጉዳይ ቢሮ ምክትል ሃላፊ ወይዘሮ ሰላማዊት አለማየሁ በጉብኝት ወቅቱ ላይ እንደተናገሩት የሴቶችን ሁለንተናዊ ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ የተፈጠረውን አደረጃጀት አሁን ካለበት በላቀ ሁኔታ ማጠናከር ይገባል። ከክልል ጀምሮ እስከ ታች ድረስ ያሉ አደረጃጀቶችን በማጠናከር ሴቶች በራቸው አቅም የሚወስኑበትና መብታቸውን የሚያስከብሩበት የእኩልነት መርህን ለማስፈን ቢሮው እየሰራ መሆኑን ገልጸዋል። በኢኮኖሚው ዘርፍ ሴቶችን በተዘዋዋሪ ብድር፣ በገጠርና በከተማ የቦታ አቅርቦትና በሌሎች ልማቶች በማሳተፍ ፍትሃዊ ተጠቃሚነትን ለማስረጽ የተደረገው ጥረት ለውጥ ማምጣቱን በጉብኝቱ ማረጋገጣቸውን ተናግረዋል። በደብረ ኤልያስ በተካሄደው ጉብኝት የሴቶችን  ጥንካሬ  የተመለከትንበት ነው ያሉት ወይዘሮ ሰላማዊት ይህም ሴት ልጅ ሀላፊነቱ ከተሰጣት የማትወጣው ተግባር እንደሌለ ማሳያ ነው ብለዋል። የምስራቅ ጎጃም ዞን ሴቶች፣ ህጻናትና ወጣቶች ጉዳይ መምሪያ ኃላፊ ወይዘሮ እሌኒ አባይ በበኩላቸው መምሪያው ሴቶችን የአስተሳሳብና የአመለካከት ለውጥ እንዲያመጡ የሰራው ስራ ተስፋ ሰጪ ውጤት ታይቶበታል ። ይህም በኢኮኖሚ፣ ማህበራዊና ፖለቲካዊ ጉዳዮች በንቃት እንዲሳተፉና ፍትሃዊ ተጠቃሚነትን እንዲያረጋግጡ ምቹ ሁኔታ ፈጥሮላቸዋል ። በዞኑ አደራጃጀት ፈጥረው በገቢ ማስገኛ ስራዎች የተሳተፉ 33 ሺህ 800  ሴቶች  5ነጥብ 2 ሚሊየን ብር መቆጠባቸውን በማሳያነት ጠቅሰዋል ። ሴቶቹ መቆጠብ የቻሉት በእንስሳት ሀብት፣ በአትክልትና ፍራፍሬ፣ በመስኖ ልማት፣ በባልትናና በመሰል የስራ ዘርፎች ተሰማርተው ውጤታማ ተግባር በማከናወን መሆኑን የመምሪያ ኃላፊዋ ተናግረዋል ። በደብረኤሊያስ ወረዳ በቁርቁር ቀበሌ በአትክልትና ፍራፍሬ ልማት ከተሰማሩት ሴቶች መካከል ወይዘሮ አስሬ ታየ በሰጡት አስተያየት ከሁለተ ዓመት በፊት 16 ሆነው በመደራጀት  ወደስራ መግባታቸውን አውስተዋል። በተሰጣቸው ሁለት ሄክታር መሬት ላይ አትክልትና ፍራፍሬና አልምተው በመሸጥ የእለት ወጪያቸውን ከመሸፈን ባሻገር በጋራ 176 ሺህ ብር መቆጠብ መቻላቸውን ገልጸዋል። አሁን ላይ ገቢያቸው እያደገ በመመጣቱ የእህል ወፍጮ ለመትከል ቦታ እየጠቁ መሆኑን ተናግረዋል። በዚህ ዓመት ደግሞ ከአቮካዶ ልማት ከአንድ ሚሊየን ብር በላይ ገቢ እንደሚጠብቁ አብራርተዋል። የዚሁ ወረዳ የጫጎ ቀበሌ ነዋሪ ወይዘሮ ፈንታየ አለፈ በበኩላቸው ከ20 በላይ ሴቶች ሆነው በጓሮ አትክልት ልማት በመሳተፍ ተጠቃሚ መሆናቸውን ተናግረዋል። በአንድ ሄክታር ተኩል ማሳ ላይ በመስኖ ልማት በመሳተፍ ጎመን፣ ካሮት፣ ቀይ ስርና ቃሪያ በማልማት በዓመት ከ100 ሺህ ብር በላይ ገቢ እያገኙ መሆኑን ገልፀዋል። ከአባላቱ መካከል አንዳንዶቹ ከተማ ላይ ቤት ሰርተው በማከራየት ተጠቃሚ መሆናቸውን ጠቅሰው እሳቸውም ልጃቸውን በግል ኮሌጅ  ከፍለው በማስተማር ላይ መሆናቸውን አስረድተዋል ። በዞኑ ከ16 ሺህ በላይ  የሴቶች ልማት ቡድን አደራጀጀት ተፈጥሮ የአካበቢያቸውን ጸጋ መሰረት በማድረግ በተለያዩ የገቢ ማስገኛ ፕሮግራሞች ተሳታፊ መሆናቸውን ከመምሪያው የተገኘው መረጃ ያመላክታል ።  
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም