`` የኢህአዴግን ውህደት አሃዳዊ ነው የሚሉ 'የብሔረሰቦችን ስሜት ለመኮርኮርና እንደተገፉ ለማስመሰል የሚቀርብ አነጋገር ነው``

95

አዲስ አበባ ኢዜአ ህዳር 3/2012 የፓርቲዎች ውህደት አቅምን ለማጠናከር ቢጠቅምም "የኢህአዴግና አጋሮቹ መዋሀድ ግን ፌዴራሊዝም ስርዓትን ያሳጣል" ሲሉ የወላይታ ህዝብ ዴሞክራሲያዊ ድርጅት ሊቀ መንበር ገለጹ።

የኢህአዴግና አጋር ፓርቲዎች ውህደት መፈጸም ኢትዮጵያዊነትን የሚያገለግል እንጂ መንግስታዊ መዋቅሩን እንደማይለውጥ አንድ የፖለቲካ ሳይንስ ምሁር ተናገሩ።

የወላይታ ህዝብ ዴሞክራሲያዊ ድርጅት ሊቀመንበር አቶ ተክሌ ቦረና፤ የፖለቲካ ፓርቲዎች መሰባሰብ፣ መጣመር፣ ግንባር መፍጠርና መዋሃድ የፓርቲዎችን አቅም ለማጎልበት ከፍተኛ ፋይዳ እንዳለው ይናገራሉ።

ውህደት የእርስ በርስ ውድድርን ለማስወገድ ብሎም ህዝብን ወክሎ በፓርላማ ወንበር ለመያዝ እንደሚጠቅምም ነው የሚገልጹት።

ነገር ግን በአራት ድርጅቶች ግንባር የተፈጠረው ገዥ ፓርቲው ኢህአዴግና አጋር ፓርቲዎች "መዋኸድ አሃዳዊነትን ያመጣል፤ ቀስ በቀስ የፌዴራሊዝምን ስርዓት የሚያሳጣ ነው" ሲሉ ስጋታቸውን ይገልጻሉ።

አሁን ባለው የክልል አወቃቀር ክልሎች የራሳቸውን አስተዳድርና ህገ መንግስት ቀርፀው እየሰሩ መሆናቸውን አመልክተው፤ ውህደቱ፣ ህገ መንግስታቸው እንዲጣስ የሚያደርግ እንደሆነም ነው የሚናገሩት።

የፖለቲካ ሳይንስ ምሁር አቶ ዳያሞ ዳሌ በዚህ ሀሳብ አይስማሙም። የፓርቲና የመንግስት መዋቅሮች የተለያዩ በመሆናቸው ከፌዴራል ስርዓት ጋር አያገናኘውም፤ አሃዳዊ መንግስትም ለመመስረት የሚያስችል ምክንያት የለውም የሚል አቋም አላቸው።

የኢህአዴግና አጋር ፓርቲዎች ውህደት መፈጸም አገራዊ ፋይዳው የጎላ፣ ለኢትዮጵያዊነቱ የሚያገለግል እንጂ መንግስታዊ መዋቅሩን እንደማይለውጥ አብራርተዋል።

ኢህአዴግ አገር ሲገዛ የቆየው ከሁሉም ኢትዮጵያ የመጣ ኢትዮጵያዊ ፓርቲ ሆኖ ሳይሆን የአራት ክልሎች ፓርቲ ሆኖ መሆኑን በማስታወስ።

ውህደቱ ኢህአዴግን ሕጋዊነት የሚያላብስ መሆኑን ያመለከቱት አቶ ዳያሞ፤ ሌሎች አገራዊ ተቋማትም ከብሔር ወደ አገራዊ እንዲለወጡ ጠቀሜታ እንደሚኖረውም ተናግረዋል።

በሌላ በኩል አቶ ተክሌ በኢህአዴግ አጋርነት ላለፉት ዓመታት በክልል ገዥ ፓርቲነት የቆዩት ፓርቲዎች ከኢህአዴግ ጋር መዋሃዳቸውን ይቃወማሉ።

ከውህደት ይልቅ በኢህአዴግ ግንባር አባልነት ታቅፈው መቀጠል እንዳለባቸው ያምናሉ።

አቶ ዳያሞ የኢህአዴግን ውህደት አሃዳዊ ነው የሚሉት 'የብሔረሰቦችን ስሜት ለመኮርኮርና እንደተገፉ ለማስመሰል የሚቀርብ አነጋገር ነው' ይላሉ።

ከዚህ ውጭ "ፌዴራሊዝምን አስወግዶ አሃዳዊ ለማድረግ ነው" የሚለው ሙግት የህወሓት ፍላጎት እንደሆነ ገልጸዋል።

በ1996 ዓ.ም በተካሄደው 5ኛ ድርጅታዊ ጉባኤ ጀምሮ በተከታታይ ሲነሳ የቆየው የውህደት ጥያቄ ላይ ምላሽ ለመስጠት እንዲቻል በሁሉም የኢህአዴግ መድረኮች በውህደቱ አስፈላጊነት ላይ ስምምነት ሲያዝበት ቆይቷል።

በተለያዩ ጉባዔዎቹ ላይ በተቀመጠው አቅጣጫ መሰረት ውህደቱን በጥናት ላይ ተመስርቶ ለመፈፀም የሚያስችሉ እንቅስቃሴዎች ሲደረጉ መቆየታቸውን ከግንባሩ የተገኘው መረጃ ያመለክታል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም