አየር መንገዱ 384 ተማሪዎችን አስመረቀ

73
አዲስ አበባ ህዳር 2/2012 የኢትዮጵያ አየር መንገድ በአቪየሽን አካዳሚው ከሶስት ወር እስከ 2 ዓመት ያሰለጠናቸውን 384 ተማሪዎችን አስመረቀ። ከተመራቂዎች መካከል 65 ፓይለቶች፣ 70 ቴክኒሻን፣ 109 የበረራ አስተናጋጅ፣ 90ደግሞ  የማርኬቲንግ ባለሙያዎች ናቸው። በተጨማሪም ካሜሮን፣ ሞዛምቢክ፣ ታንዛንያን ጨምሮ ከ7 አፍሪካ አገራት የመጡ 16 ሰልጣኞች በምግብ ዝግጅት ተመርቀዋል። የአቪየሽን አካዳሚው ማኔጂንግ ዳሬክተር አቶ ሰለሞን ደበበ አቪየሽኑ በዘርፉ ያለውን የሰለጠነ የሰው ኃይል ክፍተት ለመሙላት ሰፊ ስራ እያከናወነ መሆኑን ገልጸዋል። በአፍሪካ እየጨመረ የመጣውን የአየር በረራ ትራፊክ ማኔጅመንት ስልጠና እያስተዋወቀ መሆኑንም እንዲሁ። ከዚህም በተጨማሪ ኢትዮ- አውሮፓ ኢንተርናሽናል ቢዝነስ ትምህርት ቤት ለመመስረት እየሰራ መሆኑንም አክለዋል። እነዚህና ሌሎች ተግባራትም አቪየሽኑ ወደ ዩኒቨርስቲ ደረጃ ለማደግ እያደረገ ያለውን ጥረት እንደሚያግዙም ተናግረዋል። ሁሉም ተመራቂዎች በሰለጠኑበት የሙያ መስክ ስነ-ምግባር የተላበሰና ምቾቱን የጠበቀ አገልግሎት ለአየር መንገዱ ደንበኞች እንዲሰጡ ጠይቀዋል። ተመራቂዎቹ በበኩላቸው በሰለጠኑበት ሙያ ኢትዮጵያን በማገልገልና ለአለም ለማስተዋወቅ መዘጋጀታቸውን ነው የተናገሩት። ከሩዋንዳ የመጣው ተመራቂ ሙጋቤ አይዛክ በበኩሉ ባገኘው ስልጠና ወደ አገሩ ተመልሶ እንደሚያገለግል ገልጾ በኢትዮጵያ ለነበረው ቆይታም ምስጋና አቅርቧል። የኢትዮጵያ አቪየሽን አካዳሚ ዛሬ የተመረቁትን ጨምሮ ከ7 ሺህ 300 በላይ ሰልጣኞችን በተለያዩ የአቪየሽን ሙያ መስኮች ማስመረቁ ተነግሯል።  
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም