የጋምቤላ ከተማ የድንጋይ ንጣፍ ሥራ ጥራትና ዲዛይን መጠበቅ አለበት- የምክር ቤት አባላት

50
ጋምቤላ ኅዳር 2 ቀን 2012 የጋምቤላ ከተማ የውስጥ ለውስጥ የድንጋይ ንጣፍ ሥራ ጥራቱንና ዲዛይኑን ጠብቆ መሰራት እንዳለበት የከተማው አስተዳደር ምክር ቤት አባላት አሳሰቡ፡፡ ምክር ቤቱ በ14ኛ አስቸኳይ ጉባዔው ለከተማው የመሠረተ ልማት ተቋማት ግንባታ  ከ77 ሚሊዮን ብር በላይ በጀት አጽድቋል፡፡ አባላቱ በጉባዔው ላይ እንዳስገነዘቡት ሥራው ጥራት፣ዲዛይንና በጠበቀና የከተማዋን ውበት በሚያስጠብቅ ሁኔታ ሊገነባ ይገባዋል፡፡ ከዚህ ቀደም በከተማዋ በተከናወነው ተመሳሳይ ሥራ የታዩት ችግሮች ዳግም መታየት እንደሌለባቸው በማሳሰብ። ከምክር ቤቱ አባላት መካከል አቶ ፒተር ሬክ እንዳሉት ቀደም ሲል በከተማዋ በተገነባው ጌጠኛ የድንጋይ ንጣፍ ሥራ አገልግሎት ሳይሰጥ ከመበላሸቱም በላይ፤በትራንስፖርት አገልግሎት ላይ ችግር መፍጠሩን ተናግረዋል፡፡ በመሆኑም በቀጣይ በከተማዋ የሚከናወኑ የልማት ሥራዎች ከጥራት ጋር ተያይዞ የሚታየውን ችግር ለማስቀረት ትኩረት ሊሰጥ ይገባል ብለዋል፡፡ ሌላው የምክር ቤቱ አባል አቶ ኦፔል ሉክ በበኩላቸው በከተማዋ የተሰሩ የውስጥ ለውስጥ የመንገድ ሥራዎች ዲዛይን እንዳልጠበቁ  ይናገራሉ፡፡ ይህም በከተማዋ ማስተር ፕላን አተገባበር ላይ ችግር ከመፍጠሩም ባለፈ በትራንስፖርት አገልግሎት አሰጣጥ ተፅዕኖ ማሳደሩን ገልጸዋል፡፡ በመሆኑም በቀጣይ በከተማዋ የሚከናወን የድንጋይ ንጣፍ ሥራ የከተማዋን ውበት ባስጠበቀ መልኩ መከናወን እንደሚገባው አሳስበዋል፡፡ ለምክር ቤት አባላት ኅብረተሰቡ የሰጠውን አደራ መወጣት እንደሚጠበቅባቸውና በተለይም በከተማዋ የሚከናወኑ የልማት ሥራዎች ጥራትና ዲዛይናቸው ተጠብቆ እንዲካሄዱ ድርሻችንን መወጣት አለብን ብለዋል፡፡ የከተማዋን እድገት ለማፋጠንና ውበቷን ለማስጠበቅ በተለይም በውሃ፣በኤሌክትሪክ፣በመንገድ፣በቴሌና በሌሎችም አካላት የሚከናወነው ሥራ መቀናጀት እንዳለበት የገለጹት ደግሞ ሌላው የምክር ቤቱ አባል አቶ ኩዊች ዊው ናቸው፡፡ ሌላው የምክር ቤቱ አባል አቶ ኡቻን ኡባሮ እንዳሉት በከተማዋ የሚከናወን የጌጠኛ የድንጋይ ንጣፍ ሥራ በተወሰኑ አካላት በመያዙ በወቅቱ የማይጠናቀቁበት ሁኔታ ይስተዋላል፡፡ በመሆኑም ሥራውን በተያዘለት ወቅት ለማጠናቀቅና ለወጣቶች ሥራ ከመፍጠር አንጻር በከተማዋ የሚከናወን የድንጋይ ንጣፍ ሥራ ለተደራጁ ወጣቶች የሚሰጥበት ሁኔታ እንዲፈጠር አሳስበዋል፡፡ የጋምቤላ ከተማ ማዘጋጃ ቤት ሥራ አስኪያጅ አቶ ኡሞድ ኡቻላ በድንጋይ ንጣፍ ሥራ  ከጥራትና ዲዛይን ጋር ተያይዞ ችግሮች መኖራቸውን አምነዋል፡፡ ችግሮቹ ለመፍታት ከሥራ ተቋራጮች ጋር በመነጋገገር ችግሮች እንዳይፈጠሩ ይሰራል ብለዋል፡፡ እንደ ስራ አስኪያጁ ገለጻ በከተማዋ የሚከናወኑ የልማት ሥራዎችን ለማፋጠን በተለይም ከአገልግሎት ሰጪ አካላት ጋር በቅንጅት እየተሰራ መሆኑን ገልጸዋል፡፡ ጉባዔው በከተማዋ የሚሰራውን የአምስት ኪሎ ሜትር የድንጋይ ንጣፍን ጨምሮ ለሌሎች የመሠረተ ልማት ተቋማት ግንባታ የሚውል ከዓለም ባንክና ከክልሉ መንግሥት የተገኘ ከ77 ሚሊዮን ብር በላይ በጀት አጽድቋል፡፡    
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም