የጠቅላይ ሚኒስትሩ ንግግር ለአገር ሰላም፣ እድገትና አንድነት ፋይዳው የጎላ ነው...የድሬዳዋ ነዋሪዎች

57
ድሬዳዋ ሰኔ 13/2010 ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ በወቅታዊ ጉዳይ ላይ ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ያደረጉት ገለጻ ለአገር አንድነት፣ ሰላምና እድገት ፋይዳው የጎላ መሆኑን የድሬዳዋ ነዋሪዎች ገልጹ። አስተያየታቸውን ለኢዜአ የሰጡ ነዋሪዎች የጠቅላይ ሚኒስትሩን የልማትና የመልካም አስተዳደር ውጥኖችን ለማሳካት በቁርጠኝነት እንደሚሰሩም ተናግረዋል፡፡ በድሬዳዋ የሳቢያን ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት መምህር ተስፋ ይልማ እንዳለው ዶክተር አብይ በተለያዩ የሀገሪቱ አካባቢዎች እየተስተዋሉ ያሉ የተለያዩ ችግሮችን ለመፍታት በተግባር ምላሽ እየሰጡ ያሉ መሪ ናቸው፡፡ በሕይወት ዘመናቸው ሲናፍቁት የነበረውን መሪ ተፈጥሮ በማየታቸው መደሰታቸውን የገለጹት አቶ እዮብ ረታ የተባሉ ነዋሪ በበኩላቸው ሌቦችና ሙሰኞችን ለህግ ለማቅረብ በሚደረገው እንቅስቃሴ ኃላፊነታቸውን ለመወጣት ዝግጁ መሆናቸውን ተናግረዋል፡፡ ጠቅላይ ሚኒስትሩ ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት  የሰጡት ምላሽ በአገር ሰላምና እድገት እንዲመጣ እንዲሁም በዜጎች መካካል አንድነትን ለማምጣት ጠቀሜታ የጎላ በመሆኑ እንደሚደግፉት ገልጸዋል። "የአገሪቱን የመልካም አስተዳደር፣ የልማትና የሰላም ችግሮች ለመፍታት የመጡ መሪ አግኝተናል፤ እኒህን መሪ በመደገፍ የአገሪቱን ታላቅነት ማረጋገጥ የሁላችንም ድርሻ ሊሆን ይገባል" ያሉት ደግሞ ዶክተር አብዱረህማን ሙሜ የተባሉ ነዋሪ ናቸው፡፡ እንደአርሳቸው ገለጻ ጠቅላይ ሚኒስትሩ የውጭና የአገር ውስጥ ባለሃብት በምጣኔ ሃብቱ ውስጥ ትክክለኛ ተዋናይ እንዲሆኑ መወሰናቸው በአገሪቱ ፕሮጀክቶችን ውጤታማ በሆነ መንገድ ለመፈጸም ያስችላል። ከእዚህ በተጨማሪ ሥራ እጥነትን ትርጉም ባለው መልኩ ለመቀነስ፣ ገቢን ለማዘመንና ዘመናዊ አስተዳደርን በሁሉም መስክ ለመገንባት መንገድ እንደሚከፍት ነው የገለጹት። በአንዳንድ አመራሮችና ጥቅማቸው በተነካባቸው ግለሰቦች ዜጎችን እርስ በርስ ለማጋጨት የሚደረገውን ጥረት በማምከን ዘላቂ ሰላምን ማስፈን የሁሉም ኃላፊነት ሊሆን አንደሚገባም ዶክተር አብዱራህማን ጠቁመዋል፡፡ ምስራቅ አፍሪካን በምጣኔ ሃብት፣ በማህበራዊና በፖለቲካ መሠረታዊ ጉዳዮች ላይ ለማዋሃድ የሚደረገው ጥረትና በጋራ ዓላማ ሥር የመሰባስብ ጉዳይ ለቀጠናው እድገት ወሳኝ መሆኑን የገለጹት ደግሞ የፖለቲካ ሳይንስ ባለሙያ አቶ ቢኒያም ተሰማ ናቸው፡፡ "ለኢትዮጵያና ለኤርትራ እህትማማች ሕዝቦች ዘላቂ ሰላምና የጋራ ተጠቃሚነት መትጋት የሁለቱ መንግስታት ብቻ ሳይሆን የቀጠናው አገሮች ጭምር ሊሆን ይገባል" ብለዋል፡፡ "ባለፉት ሁለት አስርት ዓመታት የተንሰራፋውን የሙስና አሰራር፣ የፍትህ መጓደል፣ ሃሳብን በነጻነት የመግለጽ ችግሮችና ሙሰኞችን በመናድና ሌቦችን በህግ ፊት ተጠያቂ ለማድረግ ጠቅላይ ሚኒስትሩ መወሰናቸው በእጅጉ አስደስቶኛል" ሲሉ የገለጹት ደግሞ የድሬዳዋ ዩኒቨርሲቲ የአራተኛ ዓመት ተማሪ ሰመረ ተስፋዬ ነው፡፡ ጠቅላይ ሚኒስትሩ ለአገር ሰላም ልማትና ብልጽግና ያላቸው ህልም እንዲሳካ ባለው እውቀትና ችሎታ ድጋፍ ለማድረግ መዘጋጀቱ ተናግሯል። "የትግራይ አርሶ አደርና ህዝብ በሙሉ ከስርዓቱ የተሻለ ተጠቃሚ የሆኑ ይመስለኝ ነበር፤ የጠቅላይ ሚኒስትሩ የፓርላማ ንግግር ይህን አመለካከቴን ለማረም ዕድል ሰጥቶኛል" ያሉት ደግሞ ወይዘሮ ኪሚያ መሀመድ ናቸው፡፡ የጠቅላይ ሚኒስትሩ ንግግር በአገሪቱ ሰላምና ልማት በዘላቂነት ለማምጣት ፋይዳ ያለው በመሆኑ የአገሪቱ ዜጎች በአንድነት በመነሳት ለተሻለች አገር ከጠቅላይ ሚኒስትሩ ጎን በመሆን እንዳለባቸውና ለእዚህም እራሳቸውም ዝግጁ መሆናቸውን አመልክተዋል፡፡ አስተያየት ሰጪዎቹ ባስተላለፉት መልዕክት በሙሰኞች ተመዝብሮ በውጭ ሀገር የተከማቸ ሀብትን የማስመለስና ሌቦችን ለህግ የማቅረብ ተግባር መፋጠን እንዳለበት ለአዜአ ተናግረዋል፡፡  
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም