የምእራብ ጎንደር አርሶ አደሮች በፍራፍሬ ልማት ውጤታማ መሆናቸውን ገለጹ

244

ጎንደር ኢዜአ ህዳር 2 ቀን 2012 በምዕራብ ጎንደር ዞን በበጋ መስኖ ልማት በአትክልትና ፍራፍሬ ዘርፍ የተሰማሩ አርሶ አደሮች ተጠቃሚነታቸውን ለማስፋት ዘንድሮ ልማቱን የበለጠ ለማጠናከር እንቅስቃሴ መጀመራቸውን ገለፁ ።

ሙዝን በኩታ ገጠም የግብርና ዘዴ በማልማት የተሻለ ገቢ እንዳገኙ የተናገሩት አርሶ አደሮቹ የሙዝ ማብሰያ መጋዘን ችግር ምርታቸውን ስለሚበላሽባቸው መፍትሔ እንዲፈለግላቸው ጠይቀዋል ።

በዞኑ የመተማ ወረዳ ወዲ ገምዞ ቀበሌ ነዋሪ የሆኑት አቶ ይበልጣል ጥላሁን በሰጡት አስተያየት ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በመስኖ ልማት በመሰማራት ሙዝና ፓፓያ በማልማት ገቢያቸውን እያሳደጉ ይገኛሉ።፡

‹‹ባለፈው ዓመት በሙዝና ፓፓያ ሽያጭ ያገኘሁት ገቢ በመኸር አርሻ ካገኘሁት ገቢ ይበልጣል፤›› ያሉት አርሶ አደሩ በመስኖ ካለሙት ሙዝና ፓፓያ ሽያጭ 40 ሺህ ብር በማግኘት ኑሮአቸውን እንዲሻሻል አግዞአቸዋል ።

በመሆኑም ቀደም ሲል አንድ ሄክታር መሬት በሙዝና ፓፓያ ማልማታቸውን አውስተው “በዚህ ዓመት ሁለት ሄክታር መሬት ለመሸፈን የጉልበት ሰራተኞችን በኮንትራት ቀጥሬ እያሰራሁ ነው” ብለዋል ።

በቋራ ወረዳ ዱባባ ቀበሌ ነዋሪ የሆኑት አርሶ አደር እሸቴ አየሁ በበኩላቸው ዓመቱን ሁሉ የሚፈስ ወንዝ ቢኖርም በመስኖ ዙሪያ የነበራቸው አመለካከት አናሳ በመሆኑ ከቲማቲምና ሽንኩርት ውጭ ቋሚ ሰብሎች እንዳላለሙ ገልጸዋል።

በዚህ ዓመት ግን ከሌሎች የመስኖ አምራቾች ጋር በመሆን አንድ ሄክታር መሬታቸውን ሙዝን በክላስተር ማልማት መጀመራቸውን ተናግረዋል፡፡

‹‹የፍራፍሬ ተፈላጊነት እያደገ በመምጣቱና አካባቢውም ለሙዝ ልማት ተስማሚ በመሆኑ በኩታ ገጠም እያለማሁ ነው›› ያሉት ደግሞ በምዕራብ አርማጭሆ ወረዳ የአብርሃ ጅራ ከተማ ነዋሪ አቶ ዋስይሁን ይግዛው ናቸው፡፡

በዞኑ ግብርናና ገጠር ልማት መምሪያ የመስኖ፣ አትክልትና ፍራፍሬ ባለሙያ አቶ ጌትነት ካሳሁን እንዳሉት አርሶ አደሩ በመስኖ ልማት ፍራፍሬ እያመረቱ በመሸጥ ተጠቃሚ እንዲሆኑ ድጋፍና ክትትል እየተደረገ ነው ብለዋል ።

ባለፈው ዓመት በዞኑ አንድ ሺህ ሄክታር የሚጠጋ መሬት በመስኖ መልማት እንደቻለ የገለፁት ባለሙያው በዚህ ዓመት ከሁለት ሺህ ሄክታር በላይ መሬት ለማልማት እየተሰራ መሆኑን ተናግረዋል፡፡

በዘይቱን፣ ማንጎ፣ ፓፓያ፣ ሙዝንና ሌሎች የቆላ ፍራፍሬዎችን በማልማት ውጤታማ እንዲሆኑ አርሶ አደሮችን የመደገፍ ስራ እየተሰራ ነው ብለዋል፡፡

በተለይም ሙዝን በኩታ ገጠም የማልማት ስራው ውጤታማ እየሆነ በመምጣቱ ባለፈው ዓመት ብቻ ከ200 ሄክታር መሬት ከ40 ሺህ ኩንታል በላይ ሙዝ በማምረት ለገበያ መቅረብ መቻሉን ተናግረዋል፡፡

በዚህ ዓመትም የመስኖ መሬት ያላቸውን አርሶ አደሮችን በማሰልጠንና በማብቃት ከ500 ሄክታር በላይ ማሳ በሙዝ ለማልማት እየተሰራ መሆኑን አስረድተዋል።

አርሶአደሮቹ ከገበያ እጥረትና የብክነት ችግር ጋር ተያይዞ የሚያነሱትን ጥያቄ ለመመለስም በዞኑ ዋና ከተማ አንድ የሙዝ ማብሰያ መጋዝን ለመገንባት አስፈላጊውን ቅድመ ዘግጅት ተጠናቋል ብለዋል።

በዞኑ ከ15 ሺህ ሄክታር በላይ በመስኖ ሊለማ የሚችል መሬት ቢኖርም እስከ አሁን የለማው ከሁለት ሺህ ሄክታር እንደማይበልጥ ከዞኑ የተገኘው መረጃ ያመላክታል።