አርሶ አደሩ የደረሱ ሰብሎችን በፍጥነት እንዲያነሳ ማሳሰቢያ ተሰጠ

76
መቐለ ጥቅምት 29/2012 - በትግራይ ክልል አርሶ አደሩ የደረሱ ሰብሎቹን በፍጥነት በመሰብሰብ ወቅቱን ያልጠበቀ ዝናብ ከሚያደርሰው ጉዳት እንዲከላከል በብሔራዊ ሚቲዎሮሎጂ ኤጀንሲ የመቀሌ ቅርንጫፍ አሳሰበ ። በቅርንጫፉ የትንበያና ቅድመ ማስጠንቀቂያ ኬዝቲም አስተባባሪ አቶ ዳርጌ ፍቃዱ ለኢዜአ እንደገለፁት በክልሉ በምዕራብ፤ሰሜን ምዕራብና ማዕከላዊ ዞኖች ወቅቱን ያልጠበቀ ዝናብ እየታየ በመሆኑ አርሶአደሮች የደረሱ ሰብሎቻቸውን በፍጥነት መሰብሰብ አለባቸው ። አሁን እየታየ ያለውን እርጥበት አዘል ነፋስ የዝናብ ምልክት በመሆኑ በደረሱ ሰብሎች ላይ ጉዳት ከማስከተሉ በፊት አርሶ አደሩ የደረሱ ሰብሎችን ከማሳ ለማንሳት ርብርብ ማድረግ እንዳለበት አሳስበዋል ። አርሶ አደሩ በአካባቢው ይጥላል ተብሎ የሚጠበቀውን የዝናብ ውሃ ሳይባክን ለመስኖ ልማት አገልግሎት ለማዋል ቀድመው በተዘጋጁ ጉድጓዶች የማጠራቀም ስራ እንዲያካሔድም አቶ ዳርጌ ምክር ለግሰዋል ። በትግራይ ክልል ግብርና ገጠር ልማት ቢሮ የቅድመ ማሰጠንቀቂያና አደጋ ዝግጁነት ዳይሬክተር አቶ ገብረእግዚአብሄር አረጋዊ በበኩላቸው ዝናቡ በሰብል ላይ ጉዳት አንዳያደርስ  አርሶ አደሮች በግብርና ኤክስቴንሽን ባለሙዎች በሚሰጣቸው ድግፍና ክትትል ቶሎ ሰብላቸውን እጭደው እንዲሰበስቡ እየተደረገ መሆኑን ገልፀዋል ። የዓቅመ ደካማ አርሶ አደሮች፣ የአገር ሽማግሌዎች፣ የሴቶችና አካል ጉዳተኞች ሰብል ደግሞ በየአካባቢው የሚገኙ ተማሪዎች፣የመንግስት ሰራተኞች፤የመከላከያ ሰራዊት አባላትና ሌሎች የሀብረተሰብ ክፍሎች በዘመቻ መልክ እንዲሰበሰብላቸው እየተደረገ ነው ብለዋል ። የ75 ዓመት የእድሜ ባለጸጋ የሆኑትና የእንደርታ ወረዳ ልዩ ስሙ ‘’መረሚእቲ’’ ቀበሌ ነዋሪ የሆኑት አርሶ አደር በርሀ አብርሃ በሰጡት አስተያየት በሁለት ጥማድ ማሳ ላይ የነበረውን የደረሰ ገብስና ስንዴ በህብረተሰቡና በሃገር መከላከለያ ሰራዊት አባላት ድጋፍ ታጭዶ በመሰብሰቡ እፎይታን እንደሰጣቸው ተናግረዋል። ሰራዊቱና ህብረተሰቡ ባይደግፉኝ ኖሮ አቅምና ገንዘብ ስሌለኝ ሰብሉን ማሳ ላይ ተበላሽቶና ባክኖ ይቀር ነበር በማለት የነበራቸውን ስጋት ገልጸዋል። አሁን ባለው የጉልበት ዋጋ በቀን ለአንድ ሰራተኛ ከ300 ብር እስከ 400 ብር ከፍዬ የደረሰውን ሰብሌን በወቅቱ ማሳጨድና መሰብሰብ አይቻለኝን ነበር ያሉት ደግሞ በትግራይ ማእከላዊ ዞን በሃገረ ሰላም ቀበሌ ነዋሪ የሆኑት ሴት አርሶ አደር መዓዛ ተካ ናቸው። ተማሪዎች፣መላው የአካባቢው ህዝብና ሌሎች አካላት ተባብረው በዘመቻ መልክ በማጨድ ለውቂያ ዝግጁ ስላደረጉልኝ ከስጋት ነፃ ሆኛለሁ ብለዋል።          
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም