ድምጸ ውሳኔው ሰላማዊ ሆኖ እንዲጠናቀቅ የድርሻቸውን እንደሚወጡ በሀዋሳ ከተማ ወጣቶች ገለጸ

84
ኢዜአ ህዳር 1/2012 በቅርቡ የሚካሄደው የሲዳማ ክልልነት ድምጸ ውሳኔ ሰላማዊ ሆኖ እንዲጠናቀቅ የድርሻቸውን እንደሚወጡ በሀዋሳ ከተማ ኢዜአ ያነጋገራቸው ወጣቶች ገለጹ። ወጣቶቹ  እንዳሉት  ድምጸ ውሳኔው ያለምንም የጸጥታ ችግር እንዲጠናቀቅ በየአካባቢያቸው ከሚገኙ የጸጥታ አካላት  ጋር በመተባበር ለመስራት ዝግጁ ናቸው። በሀዋሳ መሀል ከተማ ክፍለ ከተማ የአዲስ አበባ ቀበሌ ነዋሪ  ወጣት መስፍን አይናለም በሰጠው አስተያየት  “ባለፉትሁለት ዓመታት ተከስቶ የነበረው ችግር የሀዋሳ ከተማን ገጽታ ያበላሸና ለመዝናኛ የነበራትን ተመራጭነትያሳጣ ነበር” ብሏል። ይህንን  ለመቀልበስ ዛሬም በነዋሪውም ሆነ ወደ ሀዋሳ በሚመጣው እንግዳ ውስጥ ያለውን ስጋት ለማጥፋት ድምጸ ውሳኔው የሚኖረው ፋይዳ ከፍተኛ መሆኑን ተናግሯል። "ለሰላማዊነቱ የእድሜ እኩዮቼን በማስተባበር ጭምር ለመስራት ዝግጁ ነኝ"  ሲል ገልጿል። ወጣቱ እንዳለው ድምጸ ውሳኔው ሰላማዊ ሆኖ እንዲፈጸም በማደረግ ሀዋሳ የፍቅር ከተማ የሚለውን የቀድሞ ስያሜዋን ለመመለስ ይደግፋል። የቱላ ክፍለ ከተማ ዳቶ ቀበሌ ነዋሪ  ወጣት ይስሀቅ ሳቡሬ በበኩሉ "የሲዳማ ብሄር እንግዳ ተቀባይነትና አቃፊነት ዛሬም ቢሆን ያልጠፋና ወደፊትም አብሮት የሚኖር ነው "ብሏል። ወጣቱ በስሜታዊነት ተገቢ ባልሆነ መንገድ ከመጓዝ ይልቅ በመነጋገርና በመወያየት ችግሮች የሚፈቱበትን የጋራ እሴቶች በመጠቀም ሰላም ለማምጣት ከአባቶች የሚሰጠውን ምክር ተቀብሎ መስራት እንዳለበት አመልክቷል። የሲዳማ የክልልነት ጥያቄ ምላሽ እንዲያገኝ  በቅርቡ የሚካሄደው ድምጸ ውሳኔ ሰላማዊ እንዲሆንና ውጤቱን በጸጋ በመቀበል አብሮነትን የበለጠ ማሳደግ እንዲቻል ለመደገፍ ዝግጁ  መሆኑ ገልጿል። "ብዙዎች የሚመርጧት የሀዋሳ ከተማ አምና ተከስቶ በነበረው ችግር ምክንያት ብዙዎች በስጋት ውስጥ ናቸው" ያለው ደግሞ የመናኸሪያ ክፍለ ከተማ ነዋሪ  ወጣት እጹብ ማቲዮስ ናት። በህዝቡ ውስጥ ያለውን ስጋት ለማስወገድ  ከማንም በላይ አቅም ያለው ወጣቱ መሆኑን ገልጻ ወጣቱ በማህበራዊ ሚዲያ የሚተላለፉ የተሳሳቱ መረጃዎችን እንደወረደ በመቀበል ወደ ሁከትና ግጭት መግባት እንደሌለበት ጠቁማለች። የሲዳማ ክልልነት ድምጸ ውሳኔን ተከትለ ግጭት እንዳይከሰትና ሂደቱ  ሰላማዊ በሆነ መንገድ እንዲጠናቀቅ የድርሸዋን ለመወጣት ዝግጁ መሆኗን ተናግራለች። የሲዳማ ክልልነት ድምጸ ውሳኔ የሚካሄደው የህዳር 10/2012ዓ.ም እንደሆነ ታውቋል።  
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም