የክልሉ ሦስተኛው ዘላቂ የተፈጥሮ ሃብት ልማት ፕሮጀክት ይፋ ሆነ

63
አሶሳ ህዳር 1/ 2012 --- በቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል የወደመውን የተፈጥሮ ሃብት መልሶ ለማልማት የሚያግዝ ሦስተኛው ዘላቂ የተፈጥሮ ሃብት ልማት ፕሮጀክት ይፋ ሆነ፡፡ የክልሉ ርዕሰ መስተዳድር አቶ አሻድሊ ሃሰን ፕሮጀክቱን ዛሬ ይፋ ባደረጉበት ወቅት እንደተናገሩት በክልሉ ለኢንቨስትመንት የሚውል ሰፊ ለም መሬት፣ ተስማሚ ስነ-ምህዳር እና የተፈጥሮ ደን ይገኛል፡፡ ይሁንና ለረጅም ዓመታት ዘላቂ ተጠቃሚነትን ባላገናዘበ እና ጥንቃቄ በጎደለው የተፈጥሮ ሃብት አጠቃቀም ሀብቱ ከፍተኛ ጉዳት ሲደርስበት ቆይቷል፡፡ ችግሩን ለመከላከል በተፋሰስ ልማት ችግኝ በመትከልና በመንከባከብ የተገኘ ውጤት ቢኖርም በተፈጥሮ ሃብቱ ላይ ከደረሰው ጉዳት አንጻር ዝቅተኛ መሆኑን አስረድተዋል፡፡ ዛሬ ይፋ የተደረገው የክልሉ ሦስተኛው ዘላቂ የተፈጥሮ ሃብት አጠቃቀም ፕሮጀክት በተፈጥሮ ሃብት ላይ የሚደርሰውን ጉዳት በመቀነስ ሃብቱን በዘላቂነት መጠቀም የሚያስችል መሆኑን ነው ያመለከቱት፡፡ የባለሙያውንና የአርሶ አደሩን አቅም ከማጠናከር ባሻገር በተለይ የገጠር ወጣቶች እና ሴቶችን በአካባቢ ጥበቃ በማሳተፍ ኑሯቸውን መቀየር እንደሚያስችል አቶ አሻድሊ አስታውቀዋል፡፡ የክልሉ ግብርናና ተፈጥሮ ሀብት ቢሮ ኃላፊ አቶ ሙሳ አህመድ በበኩላቸው ፕሮጀክቱ የክልሉን 60 በመቶ ቆዳ እንደሚሸፍን የተፈጥሮ ሃብት ላይ ትኩረት አድርጎ እደሚሠራ ገልጸዋል፡፡ "በተለይ የዞን፣ ወረዳ እና ቀበሌ አመራሮች ህብረተሰቡን ያሳተፈ ቅንጅታዊ አሠራር እንዲከተሉ ያደርጋል" ሲሉም ኃላፊው ተናግረዋል፡፡ ፕሮጀክቱ በ12 ወረዳዎች እንደሚካሄድና አምስት ዓመታት እንደሚቆይ የተናገሩት ደግሞ የፕሮጀክቱ አስተባባሪ አቶ ታደሰ ቢራቱ ናቸው። ለፕሮጀክቱ ማስፈጸሚ ከዓለም ባንክ የተገኘ ከ70 ነጥብ 5 ሚሊዮን ብር በላይ በጀት የተመደበ ሲሆን ከ135 ሺህ በላይ ሰዎችን ተጠቃሚ ያደርጋል ተብሏል እንደፕሮጀክቱ አስተባባሪ ገለጻ የባለሙያዎች እና የአመራር ፍልሰትና መቀያየር እንዲሁም መመሪያና ደንብን ያልተከተለ የበጀትና የሃብት አጠቃቀም የፕሮጀክቱ ስጋቶች ተብለው ተቀምጠዋል፡፡ በፕሮጀክቱ ይፋ ማድረጊያ መድረክ ላይ ከተሳተፉ አርሶ አደሮች መካከል አንዳንዶቹ ቀደም ባሉ ፕሮጀክት በተከናወኑ የተፋሰስ ሥራዎች ተጠቃሚ መሆናቸውን ገልጸዋል፡፡ በአካባቢያቸው የወደሙ የቀርከሃ እና ሌሎችም ሃብቶች ማገገማቸውንና የመስኖ ውሃ መጠን መጨመሩን ተናግረዋል፡፡ አርሶ አደሮቹ እንደሚሉት በተፈጥሮ ሃብት ላይ ጥገኛ የነበሩ ነዋሪዎች ተደራጅተው በለሙ አካባቢዎች እንስሳት በማርባት ሥራ ተሰማርተው ተጠቃሚ ሆነዋል፡፡ በፕሮጀክቱ ከዚህ ቀደም የተካሄዱ ተግባራት ተጨባጭ ውጤት በማምጣታቸው ለውጤታማነቱ የአቅማቸውን ለማድረግ መዘጋጀታቸውንም አስታውቀዋል፡፡ ለግማሽ ቀን በተካሄደው በእዚህ የፕሮጀክት ይፋ ማድረጊያ መድረክ ላይ ከ200 የሚበልጡ ባለድርሻ አካላት ተሳትፈዋል ፡፡          
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም