በአማራ ክልል የሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶች ተደራሽነትን ለማስፋት ድጋፍ ተጠየቀ

83
አዲስ  አበባ  ህዳር  1/2012 በአማራ ክልል የሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶችን ቁጥር በማሳደግ ተደራሽነትን ለማስፋት የህብረተሰቡና ባለሃብቶች ድጋፍ እንዲጠናከር ተጠየቀ። የቢሮው ኃላፊ ዶክተር ይልቃል ከፍአለ ዛሬ ለክልሉ ምክር ቤት መደበኛ ጉባኤ ባቀረቡት ሪፖርት እንደገለጹት በክረምቱ ወቅት በህዝብና በመንግስት የተገነቡ አዲስ 27 ሁለተኛ እና 75 የአንደኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶች ዘንድሮ ስራ እንዲጀምሩ ተደርጓል። በተለይ አዲስ ስራ የጀመሩት ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶች በክልሉ ያለውን የዚሁ ደረጃ ትምህርት ቤቶች ቁጥር ወደ 593 ከፍ እንዲል አስችሏል። ሆኖም በክልሉ የሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶች ቁጥር አሁንም በቂ ባለመሆኑ በቀጣይ ተደራሽነትን ለማስፋት ህብረተሰቡና ባለሃብቶች ድጋፋቸውን እንዲያጠናክሩ ጠይቀዋል። በተለይም የሚሰጠውን ትምህርት በቴክኖሎጂ ለማሳደግ ጥረት ቢደረግም በመብራት እጥረት ምክንያት በተግባር የተደገፈ ትምህርት ለመስጠት ፈተና እንደሆነም ጠቁመዋል። አብዛኞቹ በክልሉ የሚገኙ ትምህርት ቤቶች ከደረጃ በታችና ለመማር ማስተማር ስራው የማይመቹ በመሆናቸው ይህንን ለመለወጥ አልማ ለያዘው ዕቅድ ስኬታማነት ሁሉም እንዲደግፈው ጥሪ አቅርበዋል። የምክር ቤቱ የሰው ሃብትና ቱሪዝም ልማት ቋሚ ኮሚቴ ሰብሳቢ ወይዘሮ ወርቄ አሰፋ በበኩላቸው ቢሮው በተዋረድ ዕቅዱን ቀድሞ በማቅረብና ተማሪዎችን በአጭር ጊዜ መዝግቦ ወደ ማስተር መግባቱ የሚበረታታ መሆኑን ገልጸዋል። ችግር ላለባቸው ተማሪዎች ባለሃብቶችና ወጣቶች በቁሳቁስ በመደገፍ በርካታዎች ወደ ከፍተኛ ትምህርት ተቋም እንዲገቡ መደረጉ ቋሚ ኮሚቴው በጥንካሬ መገምገሙን አስረድተዋል። "በተለይ በቅድመ መደበኛና ልዩ ፍላጎት የሚሹ ተማሪዎች አፈፃፀም ማነስና በዘርፉ የሰለጠኑ ባለሙያዎች ዕጥረት መኖር በትምህርት ተሳትፎና ተደራሽነት ላይ አሉታዊ ተፅዕኖ ማሳደሩን ደግሞ ቋሚ ኮሚቴው በዕጥረት ገምግሟል "ብለዋል። ትምህርት ቢሮው በአቀደው ልክ በቀጣይ ሊሰራ እንደሚገባም ወይዘሮ ወርቄ አሳስበዋል። የህዝብ ቁጥር በየጊዜው እየጨመረ መምጣት በሚፈለገው ልክ የትምህርት ቤቶችን ቁጥር ማዳረስ እንዳልታቻለ የተናገሩት ደግሞ የምክር ቤት አባል አቶ ገበየሁ ሙሌ ናቸው። ይህም ለትምህርት ጥራት ፈተና እየሆነ እንደሚገኝ ጠቅሰዋል። ትምህርት ቢሮው ችግሩን ለመፍታት ዘንድሮ ለጥራት መረጋገጥ የሰጠውን ትኩረት በመደገፍ የህዝብ ተመራጮች የድርሻቸውን እንዲወጡም አሳስበዋል። ሌላኛዋ የምክር ቤቱ አባል ወይዘሮ ሉባባ አብዱ ትምህርታቸውን አቋርጠው በህገወጥ መንገድ ለስደት የሚዳረጉ ተማሪዎችን ለመከላከል ቢሮው በዕቅዱ አካቶ ለወላጆች ግንዛቤ ሊሰጥ እንደሚገባ ጠቁመዋል። ከምክር ቤት አባላቱ ለተነሱ ጥያቄዎችም የትምህርት ቢሮ ኃላፊው ማብራሪያ ከሰጡ በኋላ ሪፖርቱ ፀድቋል።    
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም