የጠረፍ ንግድ መቋረጡ ለህገ ወጥ ንግድ መስፋፋት በር መክፈቱ ተጠቆመ

91
ሁመራ (ኢዜአ)   ህዳር ቀን 2012 በኢትዮጵያ እና በሱዳን ተጎራባች አካባቢዎች መካከል የነበረው የጠረፍ ንግድ መቋረጡ ለህገ ወጥ ንግድ መስፋፋት በር መክፈቱ ተገለጸ፡፡ በትግራይ ክልል ምዕራባዊ ዞን ሁመራ ከተማ በድንበር ላይ ንግድ ሥራ ተሰማርተው ሲሰሩ የነበሩ ነጋዴዎች ለኢዜአ እንደገለጹት ከሱዳን አጎራባች አካባቢዎች የድንበር ላይ ንግድ በ2004 ዓ.ም ተጀምሮ በ2008 ዓ.ም እንዲቋረጥ ተደርጓል፡፡ በጠረፍ ንግዱ የቁም እንስሳት፣ ጥራጥሬና ቅመማ ቅመም ህጋዊ በሆነ መንገድ ወደ ሱዳን ጠረፍ ከተሞች ይላኩ እንደነበር ነጋዴዎቹ ተናግረዋል፡፡ በጠረፍ  ንግድ ላይ ተሰማርተው ከነበሩ ነጋዴዎች መካከል አቶ ተስፉ ዮሐንስ እንዳሉት ህጋዊ በሆነ የንግድ ሥራ የቁም እንስሳትን ወደሱዳን በማሻገር ይነግዱ እንደነበር ገልጸዋል፡፡ በእዚህም በሁለት ዓመታት ጊዜ ውስጥ ከ2 ሚሊዮን ብር በላይ ዋጋ ያላቸው የቁም እንስሳትን ህጋዊ በሆነ መንገድ ወደሱዳን መላካቸውን ነው ያስታወሱት፡፡ "የጠረፍ ላይ ንግዱ 2008 ዓ.ም በመቋረጡ እሳቸውን ጨምሮ በስራው ላይ ይሳተፉ የነበሩ ኢትዮጵያውያን ከመጎዳታቸው በተጨማሪ መንግስት ከዘርፉ ያገኘው የነበረውን ገቢ እንዲያጣ አድርጎታል" ብለዋል፡፡ የጠረፍ ላይ ንግድ እንዲቋረጥ ቢደረግም ወደ ሱዳን የሚሻገሩ ህገ ወጥ የቁም የእንስሳትን መግታት አንዳልተቻለ የገለጹት ደግሞ በጠረፍ ንግድ ሥራ ላይ ተሰማርተው የነበሩት አቶ ሚከኤለ ከበደ ናቸው፡፡ "በሱዳን ተቀባይ የሆኑ ነጋዴዎችም ህጋዊ መንገድ ተከትለው ከሚላኩ የቁም እንስሳት ይልቅ በህገ ወጥ ንግድ የሚላከውን የቁም እንስሳት ስለሚያበረታተቱ ህገወጥነቱ እየተስፋፋ ነው" ብለዋል፡፡ በኢትዮጵያ ጉምሩክ ባለስልጣን የሁመራ ጉሙሩክ መቅረጫ ጣቢያ ሥራ አስኪያጅ ኮማንደር መሰለ ይማም በበኩላቸው በቂ የሆነና የተደራጀ የጉምሩክ ፖሊስ ኃይል አለመኖሩን ተናግረዋል። በእዚህም ድንበሩን ተሻግረው የሚከናወኑ ህገወጥ የንግድ እንቅስቃሴዎችን በሚፈለገው መጥን ለመቆጣጠር እንዳልተቻለ ነው የገለጹት። ባለፉት ሁለት ወራት በህገ ወጥ መንገድ ሊሸጋገሩ ሲሉ የተያዙ 75 ግመሎች እንዲወረሱ መደረጉን ኮማንደር መሰለ ይማም ተናግረዋል። "ህገ ወጥ የቁም እንስሳትና ሌሎች እቃዎችን ለመቆጣጠር በሚደረገው ጥረት የህብረተሰቡ ተሳትፎ ካልታከለበት ውጤታማ መሆን አይቻልም" ሲሉም ኮማንደር መለሰ አመልክተዋል፡፡    
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም