የኪነ ጥበብ ባለሙያዎች የወጣቶችን ስብእና ለመገንባት ትኩረት ሰጥተው ሊሰሩ እንደሚገባ ተገለፀ

70
አዳማ ሰኔ 13/2010 የወጣቶችን ስብዕና በመገንባት የልማቱ ተሳትፎና ተጠቃሚነታቸውን በበለጠ ለማረጋገጥ በሚደረግ ጥረት የሚዲያና ኪነ ጥበብ ባለሙያዎች ሚናቸውን ማጠናከር እንዳለባቸው የወጣቶችና ስፖርት ሚኒስቴር ገለጸ። ሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ ለሚዲያና ኪነጥበብ ባለሙያዎች በአዳማ ከተማ የሁለት ቀናት የምክክር መድረክ አዘጋጅቷል፡፡ የወጣቶችና ስፖርት  ሚኒስትር ዴኤታ ወይዘሮ ፍሬህይወት አያሌው በምክክር መድረኩ መክፈቻ ላይ እንደገለጹት የወጣቶች ስብዕናን ለመገንባት፣ የልማቱ ተሳትፎና ተጠቃሚነታቸውን በበለጠ ለማረጋገጥ በመንግስት እየተከናወኑ ያሉት ሥራዎች በሚዲያና ኪነ ጥበብ ባለሙያዎች ሊደገፉ ይገባል። በወጣቶች ስብዕና ላይ አሉታዊ ተዕፅኖ ከሚያሳድሩት መካከል ሥራ አጥነት፣ ደካማ የሥራ ባህል፣ የፈጠራ ክህሎት ውስንነትና ሌሎች ተያያዥ ችግሮች ተጠቃሽ መሆናቸውን ገልፀዋል፡፡ እነዚህን ችግሮች በመከላከል የወጣቶችን የልማት ተሳትፎና ተጠቃሚነት በበለጠ ለማረጋገጥ በሚደረግ ጥረት የሚዲያና ኪነ ጥበብ ባለሙያዎች ሚና ከፍተኛ መሆኑን ተናግረዋል፡፡ የመድረኩ አላማም የሚዲያና ኪነ ጥበብ ባለሙያዎች መንግስት በየደረጃው በሚያደርገው እንቅስቃሴ ውስጥ ግንባር ቀደም ተዋናይ በመሆን የሚጠበቅባቸውን ሀገራዊ ኃላፊነት እንዲወጡ ማድረግ መሆኑን ገልፀዋል፡፡ ወጣቶች በሀገሪቱ ማህበራዊ፣ ኢኮኖሚያዊና ፖለቲካዊ ልማት፣ ዕድገትና የለውጥ ጉዞን በማስቀጠል ሂደት  ውስጥ ሚናቸው የጎላ መሆኑን የገለጹት ደግሞ የመንግስት ኮሚዩኒኬሽን ጉዳዮች ጽሕፈት ቤት የኮሚዩኒኬሽን ጥናትና ምርምር አቅም ግንባታ ጄኔራል ዳይሬክተር አቶ ሀዱሽ ካሱ ናቸው። ወጣትነት በርካታ አካላዊ፣ ስነ ልቦናዊና ስሜታዊ ለውጦች የሚከሰቱበት የዕድሜ ክልል በመሆኑ በአግባቡ በመያዝ ማልማት ይገባል ብለዋል። የሚዲያና ኪነ ጥበብ ባለሙያዎች በሀገር ገጽታ ግንባታ ውስጥ ከሚያበረክቱት አስተዋጽኦ ባሻገር የአምራቹን ሃይል ውጤታማነት ለማረጋገጥ በሚደረገው እንቅስቃሴ ውስጥ የድርሻቸውን ሊወጡ እንደሚገባ አስገንዝበዋል። የወጣቶች ስብዕናን ለመገንባት፣ የልማቱ ተሳታፎና ተጠቃሚነታቸውን ለማረጋገጥ የሚዲያና ኪነ ጥበብ ባለሙያዎች ወሳኝ መሳሪያ መሆናቸውን ተገንዝበው በዘርፉ የሚደረገውን እንቅስቃሴ በሙያቸው፣ ክህሎትና እውቀታቸው ማገዝ ይጠበቅባቸዋል ብለዋል። መንግስት ከዘርፉ ባለሙያዎች ጋር በቅንጅት የሚያሰራ ስትራቴጅ፣ የልማት ፓኬጅዎች፣ ማኑዋሎችና አሰራሮች መዘርጋቱንም ጄኔራል ዳይሬክተሩ አመልክተዋል። በአዳማ ከተማ ለሁለት ቀናት በሚቆየው የምክክር መድረክ ላይ የሀገሪቷ የኪነ ጥበብ ባለሙያዎችና የተለያዩ የሚዲያ አካላት በመሳተፍ ላይ ናቸው፡፡ በቆይታቸውም በወጣቶች ስብዕና ልማት አገልግሎት አሰጣጥ፣ በወጣቶች ልማትና የለውጥ ስትራቴጅ፣ ብሔራዊ የወጣቶች ማካተቻ ማኑዋል ላይ በመወያየት ላይ ናቸው፡፡        
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም