ዘላቂ ሰላምን ለማስፈን መንግስት ህዝቡ ለሚያነሳቸው ጥያቄዎች ምላሽ መስጠት እንዳለበት ተመለከተ

104
ኢዜአ ጥቅምት 29/2012 በየደረጃው ዘላቂ ሰላምን ለማስፈን መንግስት በህዝባዊ ውይይት ወቅት የሚነሱ የልማትና የመልካም አስተዳደር ጥያቄዎች ትኩረት ሰጥቶ ምላሽ መስጠት እንዳለበት በጋምቤላ ከተማ አስተያየታቸውን ለኢዜአ የሰጡ ነዋሪዎች አመለከቱ፡፡ ነዋሪዎቹ እንዳሉት በአካባቢው ብሎም በሀገሪቱ  ዘላቂ ሰላምን ለማስፈንና ህዝባዊ አንድነትን ለማጠናከር መንግስት በትኩረት መስራት ይጠበቅበታል፡፡ ከአስተያየት ሰጪዎች መካከል ወጣት ጋልዋክ ቡም በህዝባዊ ውይይት ወቅት የሚነሱ ሀሳቦችን መንግስት ትኩረት አድርጎ ባለመመለሱ ችግሮች እንደገና የሚከሰቱበት ሁኔታ እንዳለ ተናግሯል፡፡ ወጣቱ እንዳመለከተው በአሁኑ ወቅት የተጀመረው ሀገራዊ ለውጥ ለማደናቀፍ የሚጥሩ አካላትን በህግ ተጠያቂ ከማድረግ አንጻር ክፍተቶች አሉ፡፡ መንግስት በየደረጃው ዘላቂ ሰላምን ለማስፈንና ህዝባዊ አንድነቱ ተጠናክሮ እንዲቀጥል በህዝባዊ ውይይት ወቅት የሚነሱ የልማትና የመልካም አስተዳደር ጥያቄዎች ተገቢውን ምላሽ መስጠት እንዳለበት አመልክቷል። "በህብረተሰቡ ዘንድ የተጠናከረ አንድነትና ሰላም ለማጎልበት  በየደረጃው የሚገኙ የአመራር አካላት ህዝቡን በቁርጠኝነትና በታማኝነት ማገልገል  ይገባቸዋል" ያለው ደግሞ ሌላው ወጣት ኡቦንግ ኡሞድ ነው፡፡ በተለይም ከመልካም አስተዳደር ጋር ተያይዞ የሚነሱ የህዝብ ጥያቄዎችን መንግስት በተቻለ መጠን በወቅቱ ምላሽ መስጠት እንዳለበት ጠቁሟል፡፡ በጋምቤላ ዩኒቨርሲቲ የህዝብ አስተዳደርና ልማት አመራር መምህር ሙሉጌታ ሩድ እንዳሉት የሀገሪቱን ዘላቂ ሰላም ለማስፈን መንግስት ለመልካም አስተዳደር መንስኤ የሆኑ ብልሹ አሰራሮችን ማስተካከል አለበት፡፡ በተለይም የህግ በላይነትን ለማረጋገጥ መንግስት ችግር የሚፈጥሩ አካላት ላይ በህጉ መሰረት እርምጃ መውሰድ ይጠበቅበታል፡፡ መምህር ሙሉጌታ እንዳሉት ህዝብ ለህዝብ የሚደረገው ውይይትም ተጠናክሮ መቀጠሉ በተለይም ያሉትን ችግሮች ነቅሶ ለማውጣት ምቹ ሁኔታ ይፈጥራል፡፡ ሌላው አስተያየት ሰጪ አቶ ኡቦንግ አኳይ በበኩላቸው “የክልሉን ብሎም የሀገሪቱን ዘላቂ ሰላም ለማስፈን የአመራር አካላት ህዝቡን በእኩልነትና በፍትሃዊነት ማገልገል ይገባቸዋል” ብለዋል፡፡ ህብረተሰቡም ለወንጀሎኞች መደበቂያና መሸሸጊያ ከመሆን ይልቅ ለህግ አሳልፎ በመስጠት ለሰላም ዘብ መቆም እንዳለበትም ጠቁመዋል፡፡ ሌላዋ የከተማዋ ነዋሪ ወይዘሮ ኑኑ ኡጉድ “መንግስትም ህዝቡ የሚያነሳቸውን የልማት ጥያቄዎች በተለይም ከወጣቶች ሥራ አጥነት ጋር ተያይዞ ያሉትን ችግሮች በትኩረት ሊመለከታቸው ይገባል” ብለዋል፡፡ ለሰላምና አንድነት ሁሉም የህብረተሰብ ክፍል የድርሻውን መወጣት እንዳለበትም አመልክተዋል፡፡ የጋምቤላ ክልል የሰላምና ጸጥታ ጉዳዩች ቢሮ ምክትል ኃላፊ አቶ ኡቶው ኡኮት እንዳሉት በክልሉ ዘላቂ ሰላምን ለማምጣት በትኩረት እየሰራ ነው፡፡ በተለይም ህብረተሰቡ የሰላም ባለቤት መሆኑን በመረዳት እያደረጋቸው ባሉት ውይይቶች የሚያነሳቸውን  ሀሳቦች በግብዓቶችን በመውሰድ የክልሉ መንግስት ምላሽ ለመስጠት እየሰራ መሆኑን አብራርተዋል።  
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም