የክልሉን ሰላም በዘላቂነት ለማረጋገጥ አመራሩና የጸጥታ አካላት በትኩረት መሥራት አለባቸው- የምዕራብ ዕዝ

76
ጥቅምት 29 / 2012 ዓም የጋምቤላ ክልል ሰላምን በዘላቂነት ለማረጋገጥ በየደረጃው የሚገኙ የአመራርና የጸጥታ አካላት በትኩረት እንዲሰሩ የምዕራብ ዕዝ ዋና አዛዥ ሜጀር ጀኔራል መሰለ መሰረት አሳሰቡ። የክልሉ የመጀመሪያው ሩብ ዓመቱ የጸጥታ ሥራዎች እቅድ አፈፃፀም ግምገማ ባለድርሻ አካላት በተገኙበት በፍኝዶ ከተማ ተካሄዷል። ሜጀር ጀኔራል መሰለ በግምገማ መድረኩ እንደተናገሩት የክልሉን ሰላም አስተማማኝ ለማድረግ ባለድርሻ አካላት ሊረባረቡ ይገባል። ክልሉ ባለፉት ሦስት ዓመታት ከሌሎች የአገሪቷ አካባቢዎች በተሻለ ሰላሙን አስጠብቆ መቆየቱንና በተለይም ሕዝቡ በነፈሰበት ያልነፈሰና በማህበራዊ ሚዲያዎች ያልተወናበደ መሆኑን ተናግረዋል። ይሁን እንጂ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ የአካባቢው ማህበረሰብ መገለጫ ያልሆኑ ሥርዓተ አልበኝነት፣ ስርቆት፣ ዝርፊያና ሌሎች ወንጀሎች በተለይም በከተሞች አካባቢ እየተበራከተ መምጣቱን ገልጸዋል። ስለሆነም እነዚህን ችግሮች በየደረጃው የሚገኙ የአመራርና የጸጥታ አካላት በመከላከል የሕዝቡን ሰላምና ደህንነት ለማስጠበቅ በትኩረት እንዲሰሩ አሳስበዋል። በተጨማሪም በክልሉ የተስፋፋውን ሕገ-ወጥ የጦር መሳሪያዎች ዝውውርና ኮንትሮባድን እንቅስቃሴ ባለድርሻ አካላት ችግሩን ለማስቀረት በጋራ እንዲሰሩ ጠይቀዋል። የአገር መከላከያ ሠራዊት ከክልሉ ጸጥታ አካላት ጋር በመቀናጀት የጀመረውን የጸጥታ ማስከበር ሥራ ያጠናክራል ብለዋል። የክልሉ ሰላምና ጸጥታ ጉዳዮች ቢሮ ኃላፊ አቶ ቶማስ ቱት በዚሁ ጊዜ እንዳሉት በክልሉ ቀደም ሲል የነበሩ የብሄርና የድንበር ዘለል ግጭቶች፣የከተማ ስርቆትና ሌሎች ወንጀሎችን በማስቀረት ውጤቶች መመዝገባቸውን ገልዋል። ከመድረኩ ተሳተፊዎች መካከል አቶ ኩራን ግምት በሰጡት አስተያየት በተለይም ሕገ ወጥ የጦር መሳሪያዎችና የኮንተሮባንድ መውጫና መግቢያ በሮች ላይ ቁጥጥር እንደሚጠናከር ተናግረዋል። ሕገ-ወጥ ጦር መሳሪዎችያ ዝውውርና የኮንትሮባንድ እንቅስቃሴን መግታት ያልተቻለው ኅብረተሰቡን ባሳተፈ መልኩ ባለመሰረቱ ነው ያሉት ደግሞ ሌላው ተሳታፊ አቶ ዶራር ኩም ናችው። በመሆኑም በቀጣይ የሕዝቡን ተሳትፎ ማጠናከር ችግሩን መከላከል ይገባል ብለዋል።    
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም