ለውጭ ከተላከ ቡና ከ231 ሚሊዮን የአሜሪካን ዶላር በላይ ገቢ ተገኘ

91
አዳማ ኢዜአ/ ጥቅምት 29 ቀን 2012፡- በዘንድሮው የመጀመሪያው ሩብ የበጀት ዓመት ለውጭ ገበያ ከተላከ ቡና ከ231 ሚሊዮን የአሜሪካን ዶላር በላይ ገቢ መገኘቱን የቡናና ሻይ ባለስልጣን አስታወቀ። ገቢው የተገኘው ለውጭ ገበያው ከቀረበው ከ80ሺህ ቶን በላይ ቡና ሽያጭ ነው። የባለስልጣኑ ምክትል ዋና ዳይሬክተር አቶ ሙሐመድ ሸምሱ ለኢዜአ እንደተናገሩት  ዘንድሮ የቡና ዋጋ በአለም ገበያ የተሻለ ሆኖ በመገኘቱ በሩብ የበጀት ዓመቱ  ከታቀደው በላይ ቡና ማቅረብ ተችሏል። ቡናው የቀረበው ለ67 ሀገራት መሆኑን ጠቅሰዋል። በመጀመሪያው ሩብ የበጀት ዓመት ለውጭ ገበያ ለማቅረብ ታቅዶ የነበር  74ሺህ 489 ቶን ቡና ነበር። የተገኘው ገቢ ከአምናው ተመሳሳይ ወቅት ጋር ሲነፃፀር በ27 ሚሊዮን 200ሺህ  የአሜሪካን ዶላር ብልጫ ያለው መሆኑን አቶ ሙሐመድ አስታውቀዋል። በበጀት ዓመቱ ከውጭ የቡና ግብይት ከ1 ቢሊዮን የአሜሪካን ዶላር በላይ ገቢ ለማግኘት የተቀመጠውን ግብ ለማሳካት በህብረት ሥራ ማህበራትና ዩኒዬኖች በኩል እየተሰራ መሆኑን አመልክተዋል።    
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም