የሲዳማ ሕዝበ ውሳኔ የመራጮች ምዝገባ በ1 ሺህ 782 ጣቢያዎች ተጀመረ

107
ኢዜአ ጥቅምት 27/2012 በመጪው ህዳር አስር ለሚደረገው የሲዳማ የክልልነት ጥያቄ ህዝበ ውሳኔ ድምጽ ሰጪዎች ምዝገባ ዛሬ በ1 ሺህ 782 የድምፅ መስጫ ጣቢያዎች ተጀምሯል። የሲዳማ ዞን ህዝብ ግንኙነት ጽህፈት ቤት ኃላፊ አቶ ገነነ አበራ ለኢዜአ እንደገለፁት ምዝገባው ትናንት መጀመር ቢኖርበትም የምዝገባ ቁሳቁስ ርቀት ባለባቸው አካባቢዎች ሳይደርስ በመቅረቱ ለአንድ ቀን ተራዝሞ ነበር። ዛሬ በሁሉም አካባቢ ቁሳቁስ በመድረሱ በዞኑ በሚገኙ 1617 ጣቢያዎች ምዝገባው ማለዳ ላይ መጀመሩን ገልጸዋል። የሀዋሳ ከተማ አስተዳደር መንግሰት ኮሚኒኬሽን ጽህፈት ቤት ኃላፊ አቶ መልካሙ ተፈራ በበኩላቸው በሀዋሳ ከተማ በሚገኙ 165 ጣቢያዎች ምዝገባው መጀመሩን ተናግረዋል። እድሜያቸው 18 ዓመትና ከዚያ በላይ የሆናቸውና በአካባቢው ከስድስት ወራት በላይ የኖሩ ማንነታቸውን የሚገልጽ መታወቂያ በመያዝ ለ10 ቀናት በሚቆየው ለድምጽ ሰጪነት መመዝገብ እንደሚችሉ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ማስታወቁ የሚታወስ ነው።    
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም