ከምዕራብ ሐረርጌ ዞን ተፈናቃዮች ከ300 በላይ የሚሆኑት ወደ ቀያቸው ተመለሱ

75
ጥቅምት 27/2012 ከምዕራብ ሐረርጌ ዞን ተፈናቀለው በድሬዳዋ ከተጠለሉት ተፈናቃዮች መካከል ከ300 በላይ የሚሆኑት ወደ ቀያቸው ተመለሱ። ተፈናቃዮቹ ወደ ቀደመ መኖሪያቸው የተመለሱት በአካባቢያቸው አስተማማኝ ሰላም በመስፈኑ መሆኑን የድሬዳዋ አደጋ ስጋት አመራር ማስተባበሪያ ጽህፈት አመልክቷል። በጽህፈት ቤቱ የአደጋ ስጋት ዳይሬክተር አቶ መሐመድ ኡስማን እንዳስረዱት ተመላሾቹ በሶማሌና በኦሮሚያ ክልሎች መካከል በተፈጠረው ግጭት ሳቢያ ተፈናቅለው ነበር ። ተፈናቃዮቹ ላለፉት ሁለት ዓመታት በድሬዳዋ ሚሌኒየም ፓርክና በወጣቶች ማዕከል ተጠልለው የምግብ፣የሕክምናና ሌሎች ድጋፍ ሲደረግላቸው መቆየቱን አመልክተዋል፡፡ ''ከተጓዙት በተጨማሪ 223 ቤተሰቦች ወደ ኤረር ተመልሰዋል። በተበጣጠሰ መንገድም ወደ ሶማሌ ክልል በፈቃዳቸው የተጓዙ አሉ'' ብለዋል፡፡ ለተመላሾቹ የምግብና የትራንስፖርት ወጪ እንደተሸነፈላቸውገልጸዋል። ከምዕራብ ሐረርጌ የዞንና የወረዳ አመራሮች ጋር በተደረገ ውይይት ለዘላቂ ሕይወታቸው መቋቋሚያ ድጋፍ እንደሚያደርግላቸው ከስምምነት ላይ መደረሱንም አስታውቀዋል፡፡ ከሶማሌ ክልል መንግሥት ጋር በመጠለያ የሚገኙ ከአንድ ሺህ በላይ የሚሆኑ ተወላጆችን ጉዳይ በአጭር ጊዜ ውስጥ መፍትሄ በመስጠት መጠለያው እንደሚዘጋ ተናግረዋል፡፡ አርሶ አደር ኢድሪስ ሙክታር መንግሥት በመጠለያው በቆዩበት ወቅት ያደረገውን ድጋፍ ለዘላቂ ሕይወታችን መቋቋሚያም በመስጠት እንዲያጠናክርላቸው ጠይቀዋል፡፡ ከሁለት ወራት በፊት የተፈናቀልኩበትን መኖሪያዬን ሄጄ አይቻለሁ። ሁሉም ነገር ወደ ቀድሞው ተመልሷል ያሉት ደግሞ ወይዘሮ ዘሃራ አብዱላሂ ናቸው፡፡ ''የምጓዘው ወደ ሐብሮ ወረዳ ቁፋ ቀበሌ ነው፤ ጊዜው ደርሶ ወደ ቤቴ ለመመለስ መኪናው ላይ ስወጣ ደስታ ተሰምቶኛ የሐብሮ ወረዳ ድጋፍ እንዳይለየን እንጠይቃለን'' በማለትም አስተያየታቸውን ሰጥተዋል።፡፡    
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም