ለፈጠራ ውጤቶች ስራ ላይ መዋል ኅብረተሰቡ ኃላፊነት ሊወስድ ይገባል – የትምህርት ሚኒስቴር

2233

አዲስ አበባ ኢዜአ ጥቅምት 26 ቀን 2012 ኅብረተሰቡ የተማሪዎች የፈጠራ ውጤቶች ስራ ላይ እንዲውሉ የበኩሉን ድጋፍ ማድረግ እንደሚገባው የትምህርት ሚኒስቴር አስገነዘበ።

በሚኒስቴሩ፣ በኢትዮጵያ ሳይንስ አካዳሚ፣ የሳይንስና ከፍተኛ ትምህርት ሚኒስቴርና በአጋር አካላት የተዘጋጀ አገር አቀፍ የተማሪዎችና የመምህራን የፈጠራ ስራ አውደ ርዕይ ዛሬ ተከፍቷል።

በአውደ ርዕዩ በ200 ተማሪዎች፣ በ11 መምህራንና በ10 የሳይንስ፣ ቴክኖሎጂ፣ ኢንጂነሪንግና ሂሳብ ማዕከላት የተዘጋጁ የፈጠራ ውጤቶች ቀርበዋል።

ዓለም አቀፉን የሳይንስ ቀን ምክንያት በማድረግ የተዘጋጀው አውደ ርዕዩ ዕለቱ በኢትዮጵያ ለ4ኛ በዓለም ደግሞ ለ17ኛ ጊዜ የተዘጋጀ ነው።

የፈጠራ ስራዎችን የማበረታታት ዓላማ የያዘው ይህ አውደ ርዕይ ለፈጠራ ባለሙያዎችም ልምድ የመለዋወጥ ዕድል እንደሚፈጥር የትምህርት ሚኒስትር ዴኤታዋ ወይዘሮ ጽዮን ተክሉ ተናግረዋል።

በመምህራንና በተማሪዎች የሚቀርቡ የፈጠራ ስራዎችን አገልግሎት ላይ ለማዋል የሁሉንም የኅብረተሰብ ክፍል ትብብር የሚጠይቅ መሆኑንም ነው የገለጹት።

የገንዘብ፣ የዕውቀት፣ የግብዓትና ሌሎች ድጋፎችን በማድረግ የፈጠራ ውጤቶች ስራ ላይ እንዲውሉ ኃላፊነት የመውሰድን ተገቢነትም አውስተዋል።

የኢትዮጵያ ሳይንስ አካዳሚ ፕሬዚዳንት ፕሮፌሰር ጽጌ ገብረማርያም በበኩላቸው አካዳሚው በሳይንስ ዘርፍ የተለያዩ ምክረ ሀሳቦችን በማዘጋጀት ባለድርሻ አካላትን የማማከር ስራ እየሰራ እንደሚገኝ ገልጸዋል።

የሳይንስ መስክ የአገሪቷን ኢኮኖሚያዊ ዕድገት ለማፋጠን ዋና መሳሪያ መሆኑን ገልጸው በመስኩ የምርምር ማዕከላትን ለማስፋፋት የባለ ድርሻና አጋር አካላት ርብርብ እንደሚያስፈልግ ጠቁመዋል።

የሳይንስና ከፍተኛ ትምህርት ሚኒስቴር ተወካይ ዶክተር ኤባ ማጂና ሚኒስቴሩ አዳዲስ አደረጃጀቶችን በማዋቀር ለሳይንስ ዘርፍ ልዩ ትኩረት መስጠቱን ተናግረዋል።

በአገሪቷ የሳይንስ ዘርፉን ዕድገት ለማጎልበት ዝቅተኛ የሆነውን የሳይንስ፣ ቴክኖሎጂ፣ ኢንጂነሪንግና ሂሳብ ማዕከላት ተደራሽነት ለማሻሻልም ከአጋር አካላት ጋር እየተሰራ መሆኑን ገልጸዋል።

በከፍተኛ ትምህርት ተቋማት የስራ ፈጠራ ክህሎትን ለማዳበር የሚያስችሉ አዳዲስ የትምህርት አይነቶች መሰጠት መጀመሩንም አክለዋል።