የግብፅ ፓርላማ በሀገሪቱ ተጥሎ የቆየውን የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ለ10ኛ ጊዜ አራዘመ

263

ኢዜአ ጥቅምት 26/2012 የግብፅ ፓርላማ በሀገሪቱ ውስጥ ሽብርተኝነትን ለመዋጋት ያስችለው ዘንድ ጥሎት የቆየውን  የአስቸኳይ ጊዜ  አዋጅ ለተጨማሪ ሶስት ወራት እንዲራዘም መወሰኑን ሚዲል ኢስት ሞኒቴር ዘገበ።

በመላ ግብፅ ያለው ወቅታዊ ሁኔታ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁን ለማራዘም የሚያስገድድ መሆኑን በፓርላማው መገለጹን ዘገባው አመላክቷል።

ጠቅላይ ሚኒስትር ሙስጣፋ ማዲቦል ለሀገሪቱ ፓርላማ ባደረጉት ንግግር “የጨለማ ሀይሎች በአረብ ክልል እና በመካከለኛው ምስራቅ የተፈጠረውን ብጥብጥ በንጹሃን ዜጎች ላይ እንዲሁም በጦር ኃይሎች አባላት አስከፊ ድርጊቶችን በመፈፀም ግብፅን እንዳትረጋጋ የማደረግ ተስፋ አላቸው ሲሉ መናገራቸውንም አካቷል፡፡

የአስቸኳይ ግዜ አዋጁ በመላ ሀገሪቱ ተግባራዊ እንደሚደረግ ተገልጿል።

በአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ መሰረት የግብፅ ባለስልጣናትን ማህበራዊ ሚዲያን ጨምሮ የተለያዩ መገናኛ መንገዶችን ሊያቋርጡ እንደሚችሉ እና ማንኛውንም ተጠርጣሪ የፖሊስ ኃይል በቁጥጥር ስር እንዲያውሉ የሚፈቅድ መሆኑን ዘገባው አመላክቷል።

የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁን ለመጀመሪያ ግዜ የፀደቀው እ.ኤ.አ ሚያዚያ 2017 በሰሜናዊ  ግብጽ በሚገኙ በሁለት አብያተ-ክርስቲያናት ላይ በተፈጸሙ መንታ ፍንዳታዎች ከአርባ በላይ አማኞች መገደላቸውን ተከትሎ እንደነበር የሚድል ኢስት ሞኒተር ዘገባ አውስቷል።