የብሄራዊ መረጃና ደህንነት አገልግሎት ከጣልያን የውጭ ኢንፎርሜሽንና ደህንነት ኤጀንሲ ጋር በትብብር ለመስራት ተስማሙ

77
ጥቅምት 25 / 2012ዓ.ም  (ኢዜአ) የብሄራዊ መረጃና ደህንነት አገልግሎት ከጣልያን የውጭ ኢንፎርሜሽንና ደህንነት ኤጀንሲ ጋር በትብብር ለመስራት መስማማቱ ተገለጸ። አገልግሎቱ ለኢዜአ በላከው መግለጫ እንዳስታወቀው፤ የጣልያን የውጭ ኢንፎርሜሽንና ደህንነት ኤጀንሲ ለኢትዮጵያ የሚሰጠውን የቴክኖሎጂ እና አቅም ግንባታ ስልጠና ለማጠናከር ዝግጁ ነው። የኤጀንሲው ዋና ሃላፊ ጀኔራል ሉቺያኖ ካርታ ከብሄራዊ የመረጃና ደህንነት አገልግሎት ዋና ዳይሬክተር ጀኔራል ኮሚሽነር ደመላሽ ገብረሚካኤል ጋር በሁለቱ አገሮች አቻ የመረጃና ደህንነት ተቋማት ስለሚኖረው የስራ ትብብር፣ የአፍሪካ ቀንድና አካባቢው አገሮች የፀጥታና ደህንነተ ጉዳዮች ላይ ተወያይተዋል። የጣሊያን የውጭ ኢንፎርሜሽንና ደህንነት ኤጀንሲ በተለያዩ የማህበራዊ ትስስር ገፆችን በመጠቀም የሚሰራጩትን ግጭት ቀስቃሽ፣ የጥላቻ ንግግሮችና ጽሁፎችን በተመለከተ መረጃ ለማሰባሰብና ለመመከት የሚያስችሉ የቴክኒክና የስልጠና ድጋፍ እንደሚሰጥ ዋና ኃላፊው ገልጸዋል። ለድጋፉ አፈፃፀም የጋራ የቴክኒክ ኮሚቴ እንዲዋቀርና ስራ እንዲጀምር በውይይቱ ከስምምነት ላይ ተደርሷል። የብሄራዊ የመረጃና ደህንነት አገልግሎት ዋና ዳይሬክተር ጀኔራል ኮሚሽነር ደመላሽ የጣሊያን ተቋም እየሰጠ ላለው የቴክኒክ፣ የስልጠናና የመረጃ ልወውጥ ድጋፍ ምስጋናቸውን አቅርበዋል። የሁለቱ አገሮች የመረጃና ደህንነት ተቋማት ሀላፊዎች አልሸባብና አይኤስ በአፍሪካ ቀንድና በቀጣናው የሚያደርጉትን የሽብር እንቅስቃሴዎች እንዲሁም ህገ ወጥ የሰዎች ዝውውርን፣ ድንበር ተሻጋሪ ወንጀሎችንና ህገ ወጥ የገንዘብ ዝውውርን በተመለከተ በጋራ መረጃ ለመለዋወጥና ኦፕሬሽን ለማካሄድ በሚያስችላቸው ጉዳዮች ዙሪያ በዝርዝር ተወያይተው ከስምምነት መድረሳቸውን አገልግሎቱ ያደረሰን መረጃ ያመለክታል።    
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም