“ከአንድ ብርቱ ሁለት መድኃኒቱ”

84

በሰውነት ጀምበሩ (ኢዜአ)

በመንግስት ይዞታ የተያዙ የልማት ድርጅቶችን ወደ ግል የማዛወር አስፈላጊነት እኤአ በ1980ዎች ጀምሮ እስከ 2003 የቆየ እንደነበር “ኢምፓክት ኦፍ ፕራይቬታይዜሽን”  በሚል ርዕስ የተጠና ጥናት ያሳያል። በዚህም በማደግ ላይ ያሉ አገራት በመንግስታቸው ስር የተያዙት የልማት ድጅቶችን ወደ ግል የማዛወሩ ስራ እና እንቅስቃሴ በዋናነት የአገልግሎትን ጥራት ከማሳደጉም በላይ የአገልግሎት ተደራሽነቱን በመጨመር በግብይቱ አለም ማዘመንንና ጤነኛ የሆነ የውድድር መንፈስ እንደሚፈጥር ይታመናል።

የአለም ባንክ የፖሊሲ ጥናት እንደሚያመለክተው በማደግ ላይ ያሉ 120 አገራት በዚህ በተጠቀሰው አመት ከ7ሺ በላይ ግብይቶችን ፈጽመው  የቴክኖሎጂ ሽግግር፣ የማኔጅመንት አቅምና የሥራ ዕድል ፈጠራን ጨምሮ 410 ሚሊዮን የአሜሪካ ዶላር ገቢ ወደ ካዝናቸው አስገብተዋል። በዚህም በመካከለኛው ምስራቅና ሰሜን አፍሪካ ቀጠና እኤአ 1990ዎቹ በመንግስታቸው የተያዙትን የልማት ድርጅቶች  ወደ ግል በማዛወራቸው ከ310 ግብይቶች 19 ቢሊዮን የአማሪካን ዶላር ገቢ ያስገቡ ሲሆን ከነዚህም አገራት መካከል 50 በመቶ የግብጽና 40 በመቶ የሞሮኮ ድርሻ የጎላ እንደነበር ጥናቱ ያሳያል።

ጥናቱ እንዳመለከተው በቀጠናው በፈረንጆች ሚሊንየም መባቻ በቴሌቴኮም ዘርፉ ወደ ግል የማዛወሩን ስራ የተቀላቀለው የማርኮ ቴሌኮም ሲሆን በወቅቱም 1 ነጥብ 4 ቢሊዮን የአሜሪካን ዶላር ገቢ ተገኝቶ እንደነበር መረጃው ያሳያል።  ከዚያ ጊዜ በኋላ የዘርፉ አዋጭነት በተግባር በመረጋገጡ በከፊል ወደ ግል የተዛወረው ጆርዳን ቴሌኮም 5 መቶ 8 ሚሊዮን የአሜሪካን ዶላር ገቢ የተገኘ ሲሆን እኤአ 2003 ደግሞ 12 ያክሉ የሳውዲ አረቢያ ቴሌኮምኒክሽን 4 ነጥብ 1 ቢሊዮን የአሜሪካን ዶላር ገቢ ማድረጉን በጥናቱ ላይ ተገልጿል። በዚሁ ረገድ ከሰሀራ በታች ያሉ አገራት የግሉን ዘርፍ በማበረታታት በታየበት ዕምርታዊ ለውጥ 960 ግብይቶችን በመፈጸም ወደ 11 ቢሊዮም የአሜሪካን ዶላር የሚጠጋ ማግኘት መቻላቸውና ይህም ከምስራቅ አውሮፓና ላቲን አሜሪካ ጋር ሲነጻጸር የጎላ ድርሻ እንደነበረውም የአይ ሲ ቲ አፍሪካ ጥናት ማዕከል ተመራማሪ  ዶክተር ሊሻን አደም ያስረዳሉ።

የቴሌኮም እድገት በኢትዮጵያ

በአዋጅ ቁጥር 131/52 እ.ኤ.አ. በ1952 የተመሰረተው የአሁኑ ኢትዮ ቴሌኮም በቀድሞ  መጠሪያው የኢትዮጵያ ቴሌኮሙኒኬሽን ኮርፖሬሽን  በኢትዮጵያ  ውስጥ ካሉት የመንግስት መስሪያ ቤቶች ከኢትዮጵያ አየር መንገድ ቀጥሎ ሁለተኛው ግዙፍ የመንግስት የልማት ድርጅት ሲሆን፣ ለሀገሪቱ ዘመናዊ የግንኙነት አውታር በቀዳሚነት አገልግሎት ይሠጣል።  ከዝቅተኛ የአገልግሎትና የአሰራር ሂደት የተነሳው ይህው ዘርፍ ባለፉት አመታት ጥሩ እድገት አሳይቷል፡፡ ይህንን አገልግሎት ለማዘመንና ተደራሽነቱን ለማስፋፋት  መንግስት በ1994 እና በ2005 ዓ.ም ከቻይና መንግስት የተበደረውን 3.1 ቢሊዮን ዶላር መዋዕለ ንዋይ በማፍሰስ የሞባይል ተጠቃሚዎችን ቁጥር በእጅጉ ከማሳደጉም በላይ ከ6000 ኪ.ሜ በላይ መሬት ውስጥ የተቀበረ ፋይበር በመዘርጋት አገሪቷን በዘመናዊ የኮሚኒኬሽን መስመር በመዘርጋት አሁን የደረሰበት ደረጃ ደርሷል፡፡ የኢትዮ ቴሌኮም መረጃ እንደሚያሳያው  የሞባይል ሲም ካርድ የገዙ ደንበኞች ቁጥር 65.7 ሚሊዮን የደረሰ ሲሆን ከነዚህም ውስጥ ወደ 40 ሚሊዮን የሚጠጉ የሞባይል አገልግሎት ተጠቃሚዎች ናቸው ተብሎ ይገመታል።

በተመሳሳይ የሞባይል ኢንተርኔት ተጠቃሚዎች ቁጥር በማደጉ ከሞባይል ተጠቃሚዎች ግማሾቹ (ወደ 20 ሚሊዮን የሚሆኑት) የኢንተርኔት ተጠቃሚዎች እንደሆኑ ከዚሁ ድረ ገጽ የተገኘ መረጃ ያሳያል።  ለምሳሌ በ2010 የኢትዮ ቴሌኮም ገቢ 38 ቢሊዮን ብር (1.4 ቢሊዮን ዶላር) እንደነበርና በተያዘው በጀት አመት በመጀመሪያው ሩብ ዓመት 10 ነጥብ 1 ቢሊዮን ብር ገቢ መሰብሰብ መቻሉን የተቋሙ ዋና ስራ አስፈፃሚ ወይዘሪት ፍሬህይወት ታምሩ ገልጸዋል።

በአዲስ የለውጥ ምዕራፍ ላይ የሚገኘው የኢትዮጵያ መንግስት የቴሌኮሚኒኬሽን ዘርፍን ወደ ግል ለማዛወር ዕቅድ እንዳለው ገልጿል፡፡ እንደ ጠቅላይ ሚኒስትር ዶ/ር አብይ አህመድ ገለፃ ይህ የማዛወር ሂደት የመንግስትንና የህዝብን ጥቅም በሚያስጠብቅ መልኩ እና በጥናት ተመስርቶ እንዲሆን 21 አባላት ያሉት የኢኮኖሚ አማካሪ ቡድን ተቋቁሞ የአዋጭነት ጥናቱን ሲያኬሂድ ቆይቷል።

የመንግስት የልማት ድርጅቶችን ወደ ግል የማዛወር ጥቅሞች

በመንግስት ይዞታ ስር የሚገኙ ግዙፍ አገራዊ የልማት ድርጅቶችን ወደ ግል ዘርፍ ማዛወሩ አለም አቀፋዊ ተሞክሮ ያለው ነው። በአገራችን የመጣውን አገራዊ ለውጥ መነሻ በማድረግም የኢኮኖሚ  ማሻሻያ በማድረግ የዜጎችን ሁለንተናዊ ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ አገራችን ዝግጅት ላይ ትገኛለች። በመሆኑም ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዐቢይ አህመድና መንግስታቸው ወደ ስልጣን ከመጡበት ማግስት ጀምሮ በዋናነት የውጭ ምንዛሬ ችግሩንና የብድር ዕዳ ጫናን ለመቀነስ በሚያግዝ መልኩ ትላልቅ አገራዊ ፕሮጄክቶችን በጥናት ላይ ተመርኩዞ በከፊል ወደ ግል ለማዛወር ስራዎች እየተሰሩ ይገኛሉ። ከመጀመሪያዎቹ ወደ ግል ዘርፍ ከሚሸጋገሩ የመንግስት የልማት ድርጅቶች መካከል አንዱ የሆነው ኢትዮ ቴሌኮም  ነው። ለዚህም ጠቅላይ ሚኒስትሩ ሲገልጹ ወደ ግል የማዛወር ዋና ምክንያት እያሽቆለቆለ የመጣውን የኢትዮጵያ የውጭ ምንዛሬ ማዳን ከተቻለም ተጨማሪ የውጭ ምንዛሬ ለማግኘት ነው፡፡ ምንም እንኳ የውጭ ምንዛሬ መሰረታዊ ምክንያት ቢሆንም የኢትዮ ቴሌኮም ወደ ግል የማዛወር ስራ ኢኮኖሚውን በተሻለ ደረጃ የሚያሳድግና የኢንፎርሜሽን ቴክኖሎጂ ዘርፉን በማነቃቃት የቴሌኮም ስርአትን ለመገንባት እንደሚያግዝም በዘርፉ የተደረጉ ጥናቶች ያሳያሉ። በዚህ አሰራርና ስርዓት ለመተግበር የኢትዮ ቴሌኮምን ድርሻ የሚገዙ ኩባንያዎች ፍላጎታቸውን የሚገልጹበት፣ የቴክኒክ ምዘና የሚካሄድበት፣ በሂደትም ግልጽ የጨረታ አሠራር የመከተልና የተመረጡትን በማሳወቅ ግዥውን የማስፈጸም ሥራዎች እንደሚከናወኑ የገንዘብና ኢኮኖሚ ሚኒስትር ዴኤታ ዶክተር እዮብ ተካልኝ ያስረዳሉ።

የአይሲቲ አፍሪካ ጥናት ማዕከል መረጃ እንደሚያሳየው ኢትዮጵያ ቴሌኮም በመንግስት ሞኖፖሊ ከተያዘባቸው ከአምስት የማይበልጡ ጥቂት አገሮች አንዷ ናት፡፡ የቴሌኮሚኒኬሽን አገልግሎት በግል ከሚሰጥባቸው ብዙ አገሮች እንደ ጎረቤቶቻችን ኬንያ ሶማሊያና ሱዳን የመሳሰሉት ያለው ዕድገት የሚያሳየው ይህ ዘርፍ ከመንግስት ይልቅ በግል፣ ከሞኖፖሊ ይልቅ በውድድር ላይ ቢመሰረት በጥራቱና በተደራሽነቱ የተሻለ አገልግሎት ለመስጠት ነው።

በመሆኑም በዚህ አሰራር የቴሌኮምን ዘርፍ ወደ ግል በማዛወር ኢኮኖሚውን ወደ ተሻለ ደረጃ ለማሻገር እና ተደራሽነቱን በማስፋት ጭምር የውጭ ምንዛሬን መጨመር ያስችላል የተባለ ሰፊ እንቅቃሴ በአገር ደረጃ እየተካሄደ እንደሚገኝ መረጃዎች ያስረዳሉ።  የመንግስት የልማት ድርጅቶችን ወደግል የማዛወር ሥራው የሚከናወነው በቅደም ተከትል እንደሚሆን ጠቅሰው በመጀመሪያ ዙር ኢትዮ ቴሌኮምና የስኳር ፕሮጀክቶች፣ በሁለተኛ ዙር የሃይል ማመንጫዎች፣ የባቡርና የሎጀስቲክስ ፕሮጀቶች በመጨረሻም የኢትዮጵያ አየር መንገድና ኢንዱስትሪ ፓርኮች እንደሚሆኑ ያመላከቱት ደግሞ የኢንቨስትመንት ኮሚሽን ምክትል ኮሚሽነር አቶ አንተነህ አለሙ ናቸው። እንደ ኮሚሽነሩ ገለጻ አዳዲስ የውጭ ቀጥታ ኢንቨስትመንት መሳብ ዋና ስራ ቢሆንም መዋዕለ ንዋያቸውን ያፈሰሱ ባለሀብቶች ውጤታማ ስራዎችን እንዲያከናውኑ መንከባከብና ከሰላምና መረጋጋት ጋር የተያያዙ ስራዎች መስራት እንደሚገባም አሳስበዋል። በዚህም ሙሉ በሙሉና በከፊል ወደ ግል ይዞታ ይዛወራሉ ከተባሉ የመንግሥት የልማት ድርጅቶች መካከል አንዱ የሆነውን ኢትዮ ቴሌኮም በሁለት ዘርፍ እንደሚደራጅና 51 በመቶ ድርሻ መንግሥት በመያዝ፣ የተቀረውን ድርሻ ለመሸጥ ዝግጅት ማጠናቀቁንም የገንዘብ ሚኒስቴር ገልጿል።  በዚህም በዘርፉ ለመሳተፍ  ሁለት የቴሌኮም ኦፕሬተሮችም ወደ ዘርፉ በጨረታ ተወዳድረው እንደሚገቡ መንግሥት በማስታወቁ፣ ፍላጎት ያሳዩ የውጭ ኩባንያዎች የሽያጭ ሒደቱን እየተጠባበቁ እንደሚገኙም ሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ ገልጿል።

ይህ አሰራር መተግበሩ በዋናነት የውጭ ቀጥታ ኢንቨስትመንትን በማበረታታት የውጭ ምንዛሬ ግኝትን የሚያበረታታ ቢሆንም ሌሎች ጥቅምችም አሉት። ከእነዚህ መካከልም የመጀመሪያው የግል ዘርፉ ሲስፋፋ ተጨማሪ አገልግሎቶችን ስለሚጠቀም ለስራ እድል ፈጠራና የዕውቀትና ቴክኖሎጂ ሽግግር መሰረት በማድረግ እንደሚሰራ ነው ከኢንቨስትመንት ኮሚሽን የተገኘው መረጃ የሚያሳየው።

በህዝብ ቁጥር ከአፍሪካ ሁለተኛ ደረጃ ላይ የምትቀመጠው ኢትዮጵያ ኢኮኖሚዋ በፍጥነት እያደገ ካሉ አገሮች አንዷ ናት። ይህ ዕድገቷ ግን በአንድም በሌላም ምክንያት ቀጣይነቱን ሳይጠብቅ በመቆራረጥ ሂደት ላይ ያለ ነው። ለዚህ ማሳያው ደግሞ በቴሌኮሚኒኬሽንና በፋይናንሱ ዘርፍ ምንም ትስስር የማይታይበት አገር እንደመሆኗ መጠን ይህ አሁን እየተደረገ ባለው የኢኮኖሚ ማሻሻያ የተቀላጠፈ የቴሌኮም እድገት ድህነትን ለመቀነስና የሥራ ዕድል በመፍጠሩ ረገድ የሚያደርገው አስተዋፅኦ ከፍተኛ መሆኑን የኢኮኖሚ ባለሙያዎች ያስረዳሉ። በዚህ አሰራርም የቴሌኮሚኒኬሽን ዘርፍ እድገት በእጅጉ ያንቀላፋውን የኢትዮጵያ የኢንፎርሜሽን ቴክኖሎጂ ዘርፍ ከማነቃቃቱም በላይ እንደ አካውንቲንግ፣ ኢኮኖሚክስ፣ ማኔጅመንት የመሳሰሉትን ዘርፎች ስለሚያበረታታ በመቶዎች ለሚቆጠሩ የዩኒቨርሲቲ ምሩቃን የሥራ እድል ለማመቻቸት ብሩህ ተስፋ እንዳለውም ባለሙያዎች ያስረዳሉ።

የዓለም አቀፉ የፌር ፋክስ ኩባንያ ሰብሳቢና የምጣኔ ሀብት ባለሙያ አቶ ዘመዴነህ ንጋቱ  እንደሚሉት አጠቃላይ የንግዱን ዘርፍ ወደ ግል የማዛወሩን ጥቅም ሲገልጹት በብዛት በመንግስት ሞኖፖሊ የተያዙ የልማት ድርጅቶችን ወደ ግል በመዛወራቸው ሊኖረው ከሚችሉ በርካታ ጥቅሞች መካከል እነዚህ ትላልቅ ድርጅቶች ሲገነቡም ሆነ አጠቃላይ ስራቸውን ለማስኬድ በውጭ ብድር ዕዳ ስለሆነ  የእነሱ መሸጥ ለቴሌኮም ዘርፉ የተበደረችውን የብድር ጫና የመቀነስ ጥቅሙ የጎላ ነው ይላሉ።  አክለውም ምሁሩ በጥቅሉ የቴሌኮም ሽያጩን  ወደ ግል መዛወሩ የሚቀጥለውን ብድር ከመግታቱም በላይ ከሽያጩም የሚገኘው ገቢ የአገሪቱን አጠቃላይ ብድር /እዳ/ ለመቀነስ ይረዳል ሲሉ ሙያዊ ሀሳባቸውን አብራርተዋል፡፡

እንደ አቶ ዘመዴነህ  ንጋቱ ገለጻ ከሆነ ይህ በመንግስት ደረጃ የተያዙ የልማት ድርጅቶች ወደ ግል መዛወር መቻላቸው በመካከላቸው ጤነኛ የሆነ የውድድር መንፈስ በመፍጠር የተረጋጋ የገባያ ሁኔታ እና የተረጋጋ አገራዊ ምጣኔ ሀብታዊ በማስፈን አቅርቦትን በማስፋፋት የህዝቦችን ተጠቃሚነትን ማረጋገጥ እንደሚቻል ያብራራሉ።

በተጨማሪም ሊኖረው የሚችለው ጥቅም ደግሞ በዚህ ፕራይቬታይዜሽን አሰራር በመታገዝ አጠቃላይ አሰራሩንና አመራሩን ቀልጣፋ ማድረግ፣ የቴሌኮም ወደ ግል መዛወር የድርጅቱን አመራር ወደ ግል አመራር ዘይቤ ስለሚቀይረው ቀልጣፋ አመራርና አገልግሎት እንዲሰጥ ይረዳዋል፡፡ በዚህ አጠቃላይ ከመንግስት ያላስፈላጊ የተጓተተ አሰራር (ብሮክራሲን) በማስቀረት  አዲስ የአስራርና የስራ ሞራል እንዲጎለብት እንደሚያደርግም ባለሙያዎች ያስረዳሉ። የዘርፉ ባለሙያዎች እንደሚስማሙበት በተመሳሳይ ደራጃም የፕራይቬይታዜሽንን ጥቅም ሲገልጹት የቴሌኮም ተደራሽነትና ተመጣጣኝ የአገልግሎት ክፍያ ለማግኘት፣ የቴሌኮም ወደ ግል መዛወር አዳዲስ ኢንቨስትመንትና ቴክኖሎጂን ስለማበረታት ተደራሽነቱ እየሰፋ በዛውም ልክ ተመጣጣኝነቱና ጥራቱም እያደገ ይመጣል።

በሌላ በኩል ደግሞ ቴሌኮምን ወደ ግል ማዛወር የአገልግሎቱን ተወዳዳሪነት ከመጨመሩም በተቃራኒ ወደ ግል የማዛዋወሩ ስራ በጥንቃቄ ካልተሰራ የአገሪቷ ንብረት እና ብራንድ የሆነውን ስም ወደ ግል ወስደው ስሙን ከማደብዘዝ ባለፈ የዜጎችና የአገሪቱ መረጃ ደህንነት ስጋት ላይ ይጥላል የሚሉም አልጠፉም። ከዚህ ጋር ተያይዞ ከ1987 አስከ 1994 ዓ.ም የኢትዮጵያዊያን ባለሙያዎች ጥናቶች ወደ ግል እንዲዞሩ ከተደረጉት  ድርጅቶች መካከል 223 የመንግስት የልማት ድርጅቶች ወደ ግል ዞረው ያመጡት አገራዊም ሆነ ተቋማዊ ለውጥ መገምገም ነበረበት የሚሉ ሀሳቦችም ይንሸራሸራሉ።  በሌላ በኩል ደግሞ ምንም እንኳን ይህ ወደ ግል የማዛወሩ ተግባር የውጭ ምንዛሬ እጥረትን ለመፍታት ያለመ አሰራር ቢሆንም በቅድሚያ ላለፉት አስርት አመታት በህገ ወጥ መንገዶች የወጣውን ገንዘብ ለመቆጣጠርና ለማስመለስ ጥብቅ እርምጃዎች ሳይሰራ ወደ ግል ማዛወሩ ብሩን በእጅ አዙር በማስገባት ህገ ወጥ ገንዘብን ህጋዊ አድርገው ሊጠቀሙበት ያሰቡትን ግለሰቦች በር ይከፍታል ሲሉም የተፎካካሪ ፓርቲዎች ስጋታቸውን ያቀርባሉ። በመንግስት ደረጃ ሪፖርት የተደረገው መረጃ እንደሚያሳየው እስካሁን አገራችን ወደ 20 ቢሊዮን ዶላር የአገርና የህዝብ ገንዘብ እንደተመዘበረ ተገልጿል። ስለሆነም ይህ ህገወጥ ገንዘብ እንዲመለስ በመንግስት ደረጃ ምንም አይነት አስገዳጅ ሁኔታ አልተሰራም የሚሉም አሉ። በሁለተኛ ደረጃ ከፊሉ ለአገራዊ ባለሀብቶች ይሸጣሉ መባሉ መልካም ሲሆን፣ የአገራዊ ባለሀብቶቹ የካፒታልም ሆነ የአስተዳደር ክህሎትና ተሳትፎ ተጨባጭ አቅምና ብቃት ዝቅተኛ እንደሆነ ለአዋጭነቱ የሚሞግቱት ክፍሎች ሳይቀሩ ያስታውሳሉ።

በጥቅሉ ግዙፍ የመንግስት የልማት ድርጅቶችን ወደ ግል በከፊልም ሆነ ሙሉ በሙሉ የማዛወሩ ተግባር ህዝቡን፣ ምሁራንና የሲቪክ ማህበራት ባሳተፈ መልኩ በጥናት ላይ ተመርኩዞ ቅድሚያ የአዋጭነት ጥናት በማድረግ ከተከናወነ የገንዘብ አቅም፣ አስተዳደራዊ ብቃትና ልምድ ወዳላቸው አካላት ስለሚዛወር ለአገር የኢኮኖሚ ዕድገት፣ ለዘርፎቹ መስፋፋትና ለሠራተኞች ኑሮ መሻሻል የሚኖረው ጠቀሜታ ከፍ ያለ ይሆናል። ሠላም!

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም