በትግራይ ደቡባዊ ዞን የአንበጣ መንጋው ዳግም ተከሰተ

77

ማይጨው ኢዜአ ጥቅምት 25/12 በትግራይ ደቡባዊ ዞን ዳግመኛ የተከሰተውን የአንበጣ መንጋ የመከላከል ስራ እየተካሄደ መሆኑን የኦፍላ ወረዳ ግብርናና ገጠር ልማት ጽህፈት ቤት ገለፀ።

ባለፈው ሳምንት ከአማራና አፋር አጎራባች ወረዳዎች ዘልቆ የገባው የአንበጣ መንጋ የትግራይ ክልል ህዝብ፣የሃገር መከላከያ ሰራዊት አባላት፣ተማሪዎች፣ወጣቶችና ሌሎች የህብረተሰብ ክፍሎች ባደረጉት የጋራ ርብርብ በሰብል ላይ ጉዳት ሳያደርስ መከላከል ተችሎ ነበር።

የኦፍላ ወረዳ ግብርናና ገጠር ልማት ጽህፈት ቤት ኃላፊ አቶ ሃፍቱ ኪዳነ እንደገለፁት ከትናንት ጀምሮ ደግሞ በራያ አላማጣ፣ ራያ አዘቦ እና ኦፍላ ወረዳዎች አዲስ የአንበጣ መንጋ ተከስቷል ።

የአንበጣ መንጋው  በቅንጅት የመከላከል ስራ እየተከናወነ  መሆኑንም ኃላፊው ተናግረዋል።

የአንበጣ መንጋው ከፍተኛ ቁጥር ያለውና በጣም አደገኛ እንደሆነ የተናገሩት ኃላፊው የራያ ኣላማጣ ወረዳን አልፎ ኦፍላ ወረዳ ‘’ኪዳና’’ በመባል በሚጠራ ቀበሌ መድረሱን አስረድተዋል ።

ከትናንት ማታ ጀምሮ ኬሚካል በመርጨትና በባህላዊ መንገድ በመጨፍጨፍ መንጋውን የመከላከል ስራ እየተሰራ ቢሆንም የቦታው አቀማመጥ አመቺ ባለመሆኑ ለመቆጣጠር መቸገራቸውን ተናግረዋል።

የትግራይ ደቡባዊ ዞን ግብርናና ገጠር ልማት መምሪያ ተወካይ ኃላፊ አቶ አሰፋ አስረስ በበኩላቸው፣ በራያ አዘቦ ወረዳ ከተከሰተው አዲስ የአንበጣ መንጋ  ግማሹን በኬሚካል እንዲጠፋ መደረጉን ገልፀዋል ።

መንጋውን ወደ ሌሎች ቦታዎች እንዳይዛመት ባረፈበት ቦታ ሁሉ በኬሚካል ርጭት እንዲሞት የማድረግ ስራው  ተጠናክሮ እንዲቀጥል ይደረጋል ብለዋል ።

የማይጨው፣ አላማጣ፣ ኦፍላና የመኾኒ ወረዳ ወጣቶች በቦታው ተገኝተው አንበጣውን በመከላከል ላይ እንደሚገኙ አቶ አሰፋ ተናግረዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም