ተቋማት ለሳይበር ደህንነት ትኩረት በመስጠት ሊከሰቱ የሚችሉ ጥቃቶችን እንዲከላከሉ ጥሪ ቀረበ

83
አዲስ አበባ ኢዜአ ጥቅምት 24/2012 ተቋማት ለሳይበር ደህንነት ተገቢውን ትኩረት በመስጠትና ደህንነታቸውን ለማስጠበቅ የሚረዳ ፕሮግራም በመቅረጽ ሊከሰቱ የሚችሉ ጥቃቶችን እንዲከላከሉ ጥሪ ቀረበ። በኢንፎርሜሽን መረብ ደህንነት ኤጀንሲ አዘጋጅነት የመጀመሪያው ብሔራዊ የሳይበር ደህንነት ሳምንት በአዲስ አበባ እየተከበረ ነው። "ትኩረት ለሳይበር ደህንነት" በሚል መሪ ቃል በተባበሩት መንግስታት ድርጅት የአፍሪካ ኢኮኖሚክ ኮሚሽን አዳራሽ ዛሬ የመክፈቻ መርሐ ግብር ተካሂዷል። በዓለም ለ16ኛ በኢትዮጵያ ደግሞ ለመጀመሪያ ጊዜ የሚከበረው የሳይበር ደህንነት ሳምንት ከጥቅምት 24 እስከ 30 ቀን 2012 ዓ.ም ድረስ ይቆያል። በመርሐ ግብሩ ላይ የሰላም ሚኒስትር ዴኤታ ዘይኑ ጀማል እንዳሉት፤ መንግስታዊም ሆኑ መንግስታዊ ያልሆኑ ተቋማት ለሳይበር ደህንነት ተገቢውን ትኩረት መስጠት አለባቸው። በዘርፉ ሊከሰት የሚችል ጥቃትን ለመከላከል የሚረዳ ፕሮግራም በመቅረጽ አገራዊ ኃላፊነታቸውን ሊወጡ ይገባልም ነው ያሉት። መንግስት ለሳይበር ደህንነት ልዩ ትኩረት በመስጠት በፖሊሲና በተዛማጅ የህግ ጉዳዮች ዙሪያ የሚያከናውናቸውን ተግባራት አጠናክሮ ይቀጥላልም ብለዋል። እንደ አቶ ዘይኑ ማብራሪያ የኅብረተሰቡን አስተሳሰብ በመቅረጽ ረገድ የመሪነት ሚናን የሚጫወቱት የመገናኛ ብዙሃን የሳይበር ደህንነት ጉዳይም የሁሉም ኃላፊነት መሆኑን በመረዳት የፕሮግራማቸው አካል አድርገው ሊሰሩ ይገባል። ሳይበር ለአንድ አገር ዕድገት ቁልፍ ሚና እንደሚጫወት የገለጹት ሚኒስትር ዴኤታው ትኩረት ተሰጥቶት ካልተሰራበት በአገርም ሆነ በግለሰብ ላይ አደጋ ሊያስከትል ይችላል ብለዋል። ኢትዮጵያ አምራች የሰው ኃይልን በመጠቀም ፈጣንና ቀጣይነት ያለው የኢኮኖሚ ለውጥ ለማምጣት ወጣቱ የቴክኖሎጂ ተጠቃሚና የፈጠራ ብቃት እንዲኖረው ማድረግ ይገባልም ነው ያሉት። በመሆኑም ወጣቱ በሳይበር ደህንነት ላይ ግንዛቤውና አቅሙ እንዲዳብር በየደረጃው ካሉ አካላት ጋር መስራት ያስፈልጋል ብለዋል። የኢንፎርሜሽን መረብ ደህንነት ኤጀንሲ ዋና ዳይሬክተር ወይዘሮ ኢፍራህ ዓሊ በበኩላቸው ሳይበርን በተገቢው ሁኔታ በመጠቀም ከድህነት ለመወጣት ለሚደረገው ርብርብ እንደ ማስፈንጠሪያ ኃይል በመሆን ብዙ ዕድሎችን እንደሚሰጥም አስረድተዋል። ''የሳይበር ምህዳር ተለዋዋጭ፣ ውስብስብና ድንበር የለሽ መሆኑ የሳይበር ምህዳርን በመጠቀም ሊደርስ የሚችል ጥቃትን በመከላከል በምህዳሩ ውስጥ ህልውናንና ተወዳዳሪነትን ማረጋገጥ አስቸጋሪ ነው'' ብለዋል። በኢትዮጵያ ቁልፍ መሰረተ ልማቶች፣ ተቋማት እና ዜጎች ላይ የሚደርሰው የሳይበር ጥቃት በየዓመቱ እየጨመረ መሆኑን የገለጹት ዋና ዳይሬክተሯ ችግሩን የሚመጥን የቅድመ ዝግጅትና ዘላቂ መፍትሔ  ካልተደረገ በአገሪቱ ሰላም፣ ልማትና ዴሞክራሲ ስርዓት ግንባታ ላይ ከፍተኛ ተፅዕኖ እንዳለው  አስረድተዋል። በአሁኑ ወቅት ኢትዮጵያ በተቋማትም ሆነ በዜጎች ዘንድ የቴክኖሎጂ ውጤቶችን የመጠቀም ልምድ እያደገ የመጣውን ያህል ሊያጋጥሙ የሚችሉ የሳይበር ጥቃቶችን የመከላከል አቅም እና የሳይበር ደህንነት ግንዛቤ በሚፈለገው መጠን አለማደጉን ዋና ዳይሬክተሯ አብራርተዋል። ተቋማት ስራቸውን በቴክኖሎጂ የታገዘ ለማድረግ ከሚሰጡት ትኩረት አንጻር የቴክኖሎጂውን ደህንነት ለመጠበቅና ሊያጋጥሙ የሚችሉ አደጋዎችን ለመከላከል የሚያደርጉት ጥረት እጅግ አነስተኛ በመሆኑ አደጋው የሚያደርሰው ጉዳት የከፋ ሊሆን ይችላልም ነው ያሉት። የተቋማትና የኅብረተሰቡን የሳይበር ደህንነት ንቃተ ህሊና የሚያሳድጉ ተግባራትን በማከናወን ረገድ የኢንፎርሜሽን መረብ ደህንነት ኤጀንሲ ባለፉት ጊዜያት የተለያዩ ፕሮግራሞችን በማዘጋጀት የግንዛቤ ማስጨበጫ ስራዎችን ሲሰራ መቆየቱን ተናግረዋል። በዓለም ላይ ዋና ዋና ስጋቶች ከሚባሉት ውስጥ አንዱ የሳይበር ጥቃት እንደሆነ የዓለም ኢኮኖሚክ ፎረም እንደ አውሮጳውያን አቆጣጠር በ2018 ያወጣው ዓመታዊ የስጋት ሪፖርት ያመለክታል። በ2018 ብቻ በተከሰቱ የሳይበር ጥቃቶች በዓለም ላይ 1 ነጥብ 5 ትሪሊዮን ዶላር ኪሳራ አጋጥሟል። በኢትዮጵያ የሳይበር ጥቃቱ እየጨመረ የመጣ ሲሆን በ2011 ዓ.ም ቁልፍ በተባሉ መሰረተ ልማቶችና ተቋማት ላይ 791 የሳይበር ጥቃቶች ተሰንዝረዋል። በተባበሩት መንግስታት የአፍሪካ ኢኮኖሚክ ኮሚሽን አዳራሽ በተከፈተው መርሐ ግብር አገራዊ የሳይበር ደህንነት ነባራዊ ሁኔታ እና የሳይበር ደህንነት መፍትሔዎች ላይ የፓናል ውይይት ተደርጓል። በሳይበር ደህንነት ዙሪያ የተዘጋጀ አውደ ርዕይንም የሰላም ሚኒስትር ዴኤታ አቶ ዘይኑ ጀማል ከፍተዋል።
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም