በመጪው ታህሳስ የአካል ጉዳተኞች የጎዳና ላይ ሩጫ ይካሄዳል

76

ጥቅምት 24 ቀን 2012 የሶስት ኪሎ ሜትር የአካል ጉዳተኞች የጎዳና ላይ ሩጫ ውድድር በመጪው ታህሳስ በአዲስ አበባ እንደሚካሄድ አዘጋጆቹ ገለጹ።

የጎዳና ላይ ሩጫ ውድድሩን ቲ.ኤፍ.ቲ የሚዲያና ኮሙኒኬሽን ድርጅት ከኤል.ቲ.ኤስ ጠቅላላ የስፖርትና መዝናኛ ኢቨንት ኦርጋናይዘር ጋር በጋራ አዘጋጅተውታል።

የሩጫው አስተባባሪ ጋዜጠኛ ተስፋዬ ገብረማርያም እንደገለጸው በአገሪቷ 25 ሚሊዮን አካል ጉዳተኞች እንዳሉ ቢታመንም እምቅ አቅማቸውን እንዲጠቀሙ የሚሰጣቸው ስፍራ እምብዛም ነው።

እነዚህ ዜጎች በአካል ጉዳተኝነት ውስጥ ከባድ ፈተናዎችን የሚያልፉ በመሆኑ ይህን ተጋፍጠው ከስኬት ለመድረስና ያለሙትን ግብ ለማሳካት ቆራጥነትና በራስ የመተማመን ስሜታቸውን ማጎልበት ይገባል ብሏል።

የጎዳና ላይ ሩጫው ለአረጋዊያን አካል ጉዳተኞችና ለዓይነ ስውራን መጠቀሚያ ቁሳቁሶችን ለመርዳትና በአዕምሮ ውስንነት ላይ የሚሰሩ ማኅበራትና ድርጅቶችን ለመደገፍ ያለመ መሆኑንም ገልጿል።

ይህ የጎዳና ላይ ሩጫ በዋናነት የኢትዮጵያ ቡናና የቅዱስ ጊዮርጊስ ስፖርት ክለብ ደጋፊዎች በጋራ በመሆን ለአንድ ዓላማ ድጋፋቸውን የሚያረጋግጡበትም ነው ተብሏል።

በውድድሩ ከ40-50 ሺህ የሚሆኑ ሰዎች እንደሚሳተፉ የሚጠበቅ ሲሆን አካል ጉዳተኞችን ለመደገፍ ኅብረተሰቡ የሩጫው አካል በመሆን ተሳትፎውን እንዲያረጋግጥ ጥሪ ቀርቧል።

ሶስት ኪሎ ሜትር የሚሸፍነው የሩጫ ውድድሩ መነሻና መድረሻውን ከልደታ ፍርድ ቤት ወደ መስቀል አደባባይ እንደሚያደርግም ተገልጿል።

ውድድሩ አካል ጉዳተኞችን ብቻ ሳይሆን ጉዳት የሌለባቸው የማህበረሰብ ክፍሎችንም የሚያሳትፍ ነው።

በዚህ ውድድር በፓራ ኦሎምፒክ ለሚወዳደሩና ከ1ኛ እስከ 3ኛ በመውጣት ለሚያጠናቅቁ ተሳታፊዎች ሽልማት እንደሚበረከት አዘጋጆቹ ገልጸዋል።

ታህሳስ 12 ቀን 2012 ዓ.ም የሚካሄደው የጎዳና ላይ ሩጫ "ለአካል ጉዳተኞች የቴክኖሎጂ ተደራሽነት በጋራ እንሩጥ" መሪ ሃሳቡ ነው።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም