አርሶ አደሮች ነባር የሽምብራ ዝርያዎች ምርታማነት በመዳከሙ አዳዲስ ዝርያዎች እንዲቀርብላቸው ጠየቁ

2562

ጎንደር ኢዜአ ጥቅምት 24 ቀን 2012 ነባር የሽንብራ ዝርያዎች ምርታማነታቸውን እየተዳከመ በመምጣቱ አዳዲስ ዝርያዎች እንዲቀርብላቸው በማእካለዊ ጎንደር ዞን የምእራብ በለሳ ወረዳ ሽንብራ አምራች አርሶ አደሮች ጠየቁ፡፡

የአርሶ አደሩን ችግር ለመፍታት ለአካባቢው ስነ ምህዳር ተስማሚ የሆኑ አዲስ የሽንብራ ዝርያዎችን በሁለት ዓመታት ጊዜ ውስጥ ለማቅረብ በምርምር የታገዘ ስራ እያከናወነ መሆኑን የጎንደር ግብርና ምርምር ማእከል አስታውቋል፡፡

በወረዳው አርባያ በተባለው ቀበሌ ምርምር ማእከሉ ኩታ ገጠም የሽንብራ ልማት ቴክኖሎጂን ለማስተዋወቅና ለማስፋት ባዘጋጀው የመስክ በዓል ትናንት በአርሶ አደሮች ተጎብኝቷል፡፡

በጉብኝቱ ከተሳተፉ ሽንብራ አምራቾች መካከል አርሶአደር ጥገት ሞላ በሰጡት አስተያየት ከሁለት ዓመት በፊት የመጣውን ዝርያ የተሻለ ቢሆንም ዘንድሮ ለአበባ ሲደርስ ባልታወቀ በሽታ ምርቱ መጥፋቱን ተናግረዋል፡፡

ትልቁ ሃብታችን ፣ የቤታችን ምሰሶና ለገበያ የምናቀርበው ሰብል ሽንብራ ቢሆንም አሁን ላይ በበሽታ በመጠቃቱ ምርት አልባ እያደረገን ነው ብለዋል፡፡

“በአንድ ነጥብ አምስት ሄክታር መሬት ላይ የዘራሁት የሽንብራ ሰብል በአበባ ደረጃ እያለ ሙሉ በሙሉ ወድሟል ” ያሉት ደግሞ በወረዳው የድቋና ቀበሌ ነዋሪ አርሶአደር አዝኖልኝ ባይለየኝ ናቸው፡፡

ምርምር ማእከሉ በሽታንና ተባይን ተቋቁመው ከፍተኛ ምርት መስጠት የሚችሉ አዳዲስ የሽንብራ ዝርያዎችን እንዲያቀርብላቸው ጠይቀዋል፡፡

የወረዳው ግብርና ጽህፈት ቤት ሃላፊ አቶ ፈንቴ አለባቸው በዘንድሮ የመኸር እርሻ በሽንብራ ከተሸፈነው ስምንት ሺህ ሄክታር መሬት አምስት ሺህ ሄክታሩ በበሽታ፣ በተባይና በዝናብ መብዛት ምክንያት መጎዳቱን ተናግረዋል፡፡

አድርቅ የተባለውን የሽንብራ በሽታ መቋቋም የሚችሉ የተሞከሩ ዝርያዎችን የግብርና ምርምር ማእከሉ በማቅረብ አርሶአደሩ የገጠመውን ችግር መፍታት እንደሚገባም ጠይቀዋል፡፡

የጎንደር ግብርና ምርምር ማእከል ሃላፊ አቶ አዛናው አስፋው “ደስ” የተባለው ነባር የሽንብራ ዝርያ “አስኮካይት” በተባለ በሽታ በመጠቃቱና በመውደሙ ከምርት ስራ ውጪ እየሆነ መጥቷል።

በሽታውን በኬሚካል ለማጥፋት ማእከሉ ምርምር እያካሄደ መሆኑን ጠቁመው በኩታ ገጠም የተዘራው አዲሱ ካቡሊ የተባለው የሽንብራ ዝርያ  ግን ውጤታማ በመሆኑ የማስተዋወቅና የማስፋት ስራ መጀመሩን ተናግረዋል፡፡

በሽታንና ተባይን ተቋቁመው ከፍተኛ ምርት መስጠት የሚችሉ አዳዲስ የሽንብራ ዝርያዎችን በቀጣዮቹ ሁለት ዓመታት በምርምር በማፍለቅ ወደ ወረዳው ለማስገባት ጥረት ይደረጋል ብለዋል ፡፡

በማእከላዊ ጎንደር ዞን በምርት ዘመኑ ሽንብራ አብቃይ በሆኑ አምስት ወረዳዎች 27 ሺህ ሔክታር መሬት በሽንብራ የለማ ሲሆን ከ500 ሺህ ኩንታል በላይ ምርት እንደሚጠበቅ ከዞኑ ግብርና መምሪያ የተገኘው መረጃ ያመለክታል፡፡