የሃዋሳ ግርግር ዳግም እንዳይከሰት በመከላከል ተጎጂዎችን እናቋቁማለን....የሲዳማ ብሔር ተወላጆች

50
ሀዋሳ ሰኔ 12/2010 በሲዳማ ዞን ሀዋሳና የተለያዩ አካባቢዎች የተከሰተው ሁከትና ግርግር ዳግም እንዳይፈጠርና ተጎጂዎችን መልሶ ለማቋቋም ሁሉም የሲዳማ ህዝብ እንደሚሰራ ኢዜአ ያነጋገራቸው የብሄሩ ተወላጆች ገለጹ፡፡ ከሲዳማ ዞን ሁሉም ወረዳዎች የተውጣጡ የብሄሩ ተወላጆች የሀይማኖት መሪዎች ወጣቶችና ሴቶች ዛሬ በሀዋሳ ከጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ ጋር ተወያይተዋል።፡ በውይይቱ ላይ ከዳራ ወረዳ የመጡት የሀገር ሽማግሌ አቶ አደፍርስ እስራኤል "እኛ ባላሰብነውና ባልጠበቅነው መልኩ በድንገት ተከስቶ የነበረው ግርግር አሳዛኝ ነው።" ብለዋል "ከጠቅላይ ሚንስትሩ ጋር ባደረግነው ውይይት ሁሉንም ነገር በውይይትና በዕርቅ መፍታት እንዳለብን ነግረውናል ዳግም እንዳይከሰት እኛ በማወያየት እንፈታዋለን” ያሉት የሃገር ሽማግሌው “ችግሩን  ከፈታን ሲዳማ ወደ ክብሩ ይመለሳል" ብለዋል። የሲዳማ ዞን እስልምና ጉዳዮች ሰብሳቢና የዞኑ ሀይማኖት ጥምረት ምክትል ሰብሳቢ ሀጂ ሙስጠፋ ናስር በበኩላቸው “የተከሰተው ችግር አላስፈላጊ አቅጣጫ በመከተል የመጣ ነው ለማስቆምም ጥረት አድርገናል እጃቸው ያለበትን ወጣቶችንም አሳልፈን ሰጥተናል” ብለዋል፡፡ ይህ ግርግር ለሲዳማ ህዝብ ስራውም ታሪኩም ወጉም አለመሆኑንና የሲዳማ ህዝብ ብሔርን ለይቶ የሚያጠቃ አለመሆኑን ገልጸዋል። ’’የተዘረፉ ንብረቶችም በየቤታቸው የገባ ሰዎች ፈጣሪያቸውን ፈርተው የሰውን ንብረት የሰውን ሀቅ ወደ ቦታው እንዲመለስ እንዲያደርጉ በዞኑ የሀይማኖት ተቋማት ጉባኤ ስም ጥሪዬን አስተላልፋለሁ’’ ብለዋል። የተፈናቀሉ ወገኖችን ለማቋቋምና ለማገዝ እንደሚሰሩ ገልጸው በለቅሶ በሰርግ አብረው የኖሩትን ህዝቦች ማጋጨትና ንብረታቸውን ማውደም አሳዛኝ ጉዳይና የሲዳማ ህዝብን የማይወክል በመሆኑ አውግዘዋል። ከቦና ዙሪያ ወረዳ የመጡት የሀገር ሽማግሌ አቶ ተስፋዬ ዳንጊሶ በበኩላቸው “ዛሬ ከጠቅላይ ሚንስትሩ የተሰጠው ምላሽ ሁላችንንም ያስደሰተና በጣም አርኪ ነው” ብለዋል። “በጎረቤት ሀገራት በተፈጠረ ግጭት ምን አይነት ጉዳት እንዳስከተለ ልንማርበት የሚገባና መሰል ችግር በኛ ሀገርም እንዳይከሰት ልጆቻችንን መክረን መመለስ ያለብን መሆኑን ማወቅ ያስቻለን ውይይት ነው” ብለዋል፡፡ የሀዋሳ ከተማ ነዋሪና የቢጂ አይ ሀዋሳ ስራ አስኪያጅ አቶ ዘላለም ላሌ በበኩላቸው የሰው ልጅ ሲፈጠር ብሄሩን መርጦ እንዳልተፈጠረና ቀደም ሲል በነበሩ አባቶች እንዲህ ያለ የዘር ልዩነት በፍጹም አለመታየቱን ገልጸዋል። “የሀዋሳ ከተማ የተለያየ ብሄረሰብ የሚኖርበት በመሆኑ በመስማማት በአንድነት እንዲታወቅ ያደረገው ኢትዮጵያዊ ሁሉ ነው ለዚህም ነው የፍቅር ከተማ የተባለችው” ብለዋል፡፡ ቀደም ሲል የፊቼ ጫምባላላ በዓል በሰላም ሲከበር አንድም ጉዳት እንዳልተፈጠረ ገልጸው ዘንድሮ የራሳቸው እቅድ ባላቸው አካላት በተደረገው ሴራ ይሄን ባህል የሚያጎድፍ ድርጊት መፈጸሙ የሚያሳዝን እንደሆነ አስረድተዋል። “ጉዳዩ በህግ ሲደረስበት የምናጋልጠው ይሆናል” ያሉት አቶ ዘላለም የተፈጠረው ነገር አሳዛኝና በጣም ዘግናኝ የሆነ ለሌላው አካባቢም እንዲህ አይነት ነገር መደረግ የሌለበት መሆኑን ገልጸዋል፡፡ ድርጊቱ የሀዋሳ ከተማን እድገትና የህዝቡን ፍቅር የሚያደናቅፍ በመሆኑ ይሄን ስህተት ማረም አለብን ብለዋል፡፡ አሁን ያለው የመንግስት አካሄድ በለውጥ ላይ መሆኑን እንደሚያሳይ ገልጸው ጠቅላይ ሚንስትሩ ቅንና ለለውጥ የተነሱ በመሆናቸው በተዋረድ ያሉ አመራሮችም ይህንኑ ሊከተሉ እንደሚገባ ጠቁመዋል።  
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም