ኢትዮጵያውያን አትሌቶች በዓለም አቀፍ የማራቶን ውድድሮች አሸንፈዋል

59
አዲስ አበባ  ጥቅምት  23 /2012 ኢትዮጵያውያን አትሌቶች ዛሬ በአውሮፓና እስያ በተካሄዱ ዓለም አቀፍ የማራቶን ውድድሮች ድል ቀንቷቸዋል። በቱርክ በተካሄደው የኢስታንቡል ማራቶን በሴቶች አትሌት ሂሩት ጥበቡ 2 ሰዓት ከ23 ደቂቃ ከ40 ሴኮንድ አሸናፊ በመሆን በርቀቱ ሁለተኛ የግል ምርጥ ሰዓቷን ማስመዝገብ ችላለች። አትሌት ሂሩት እ.አ.አ በ2017 በሻንጋይ ማራቶን 2 ሰዓት ከ23 ደቂቃ ከ35 ሴኮንድ በርቀቱ የግል ምርጥ ሰዓቷን ማስመዝገቧ የሚታወስ ነው። አትሌት ትዕግስት ባይቸው 2 ሰዓት ከ24 ደቂቃ ከ15 ሴኮንድ ሁለተኛ ስትወጣ በተጨማሪም እ.አ.አ በ2017 በቻይና ታይዩዋን ማራቶን በርቀቱ ያስመዘገበችውን የግል ምርጥ ሰዓቷን በ5 ደቂቃ ከ57 ሴኮንድ አሻሽላለች። በውድድሩ ኬንያዊቷ አትሌት ማውሪን ቼፕኬሞይ 2 ሰዓት ከ24 ደቂቃ ከ16 ሴኮንድ ሶስተኛ ወጥታለች። በወንዶች ኬንያዊው አትሌት ዳንኤል ኪቤት 2 ሰዓት ከ9 ደቂቃ ከ44 ሴኮንድ ሲያሸንፍ አትሌት ይታያል አጥናፉ 2 ሰዓት ከ9 ደቂቃ ከ57 ሴኮንድ ሁለተኛ ወጥቷል። ሌላኛዋ ኬንያዊ አትሌት ፒተር ክዌሞይ 2 ሰዓት ከ10 ደቂቃ ከ9 ሴኮንድ ሶስተኛ ወጥቷል። በኢስታንቡል ማራቶን ሁለቱም ጾታዎች ያሸነፉ አትሌቶች የ50 ሺህ ዶላር ሽልማት እንደሚያገኙ የቱርኩ የዜና ወኪል አናዶሉ ዘገባ ያመለክታል። ለ41 ጊዜ የተካሄደው የኢስታንቡል ማራቶን በዓለም አቀፉ አትሌቲክስ ፌዴሬሽኖች ማህበር የወርቅ ደረጃ ያገኘ ነው።       በሌላ በኩል ዛሬ በቻይና የቤጂንግ ማራቶን በሴቶች አትሌት ሱቱሜ አሰፋ 2 ሰዓት ከ23 ደቂቃ ከ31 ሴኮንድ አሸናፊ ሆናለች። አትሌት ሱቱሜ በዚህ ውድድረ እ.አ.አ በ2016 በዱባይ ማራቶን ያስመዘገበችውን የርቀቱን የግል ምርጥ ሰዓቷን በ29 ሴኮንድ አሻሽላለች። ቻይናዊቷ አትሌት ሊ ዢዋን 2 ሰዓት ከ29 ደቂቃ ከ6 ሴኮንድ ሁለተኛ ደረጃን ስትይዝ አትሌት ሙሉ ሰቦቃ በ2 ሰዓት ከ29 ደቂቃ ከ9 ሴኮንድ ሶስተኛ መውጣቷን የቻይናው ዜና ወኪል ዢንዋ በድረ ገጹ አስፍሯል። በወንዶች ኬንያውያኑ አትሌቶች ማቲው ኪሶሪዮ፣ ሰለሞን ኪርዋ እና ኢማኑኤል ሩቶ በቅደም ተከተል ከአንድ እስከ ሶስት በመውጣት በበላይነት አጠናቀዋል። በሁለቱም ጾታዎች ያሸነፉት አትሌቶች 40 ሺህ የአሜሪካን ዶላር ሽልማት ያገኛሉ። በወንዶች ውድድር ያሸነፈው አትሌት ማቲው ኪሶሪዮ የቦታውን ክብረ ወሰን በማሻሻሉም ተጨማሪ የ20 ሺህ ዶላር ሽልማት ያገኛል ። ለ39ኛ ጊዜ የተካሄደው የቤጂንግ ማራቶን በዓለም አቀፉ አትሌቲከስ ፌዴሬሽኖች ማህበር የወርቅ ደረጃ የተሰጠው ውድድር ነው። በተጨማሪም ዛሬ ከቀኑ 10 ሰዓት ከ30 ደቂቃ ላይ በሚካሄደው የኒው ዮርክ ማራቶን በወንዶች አትሌት ሌሊሳ ዴሲሳ የማሸነፍ የቅድሚያ ግምቱን አግኝቷል። ከአንድ ወር ገደማ በፊት በኳታር ዶሃ በተካሄደው 17ኛው የዓለም አትሌቲክስ ሻምፒዮና በማራቶን የወርቅ ሜዳሊያ ያገኘው አትሌት ሌሊሳ ያለፈው ዓመት የኒው ዮርክ ማራቶን አሸናፊም ነበር። ባለፈው ዓመት የኒው ዮርክ ማራቶን አትሌት ሌሊሳን በመከተል ሁለተኛ የወጣው አትሌት ሹራ ቂጣታ በውድድሩ ያሸንፋሉ ተብለው ከተጠበቁ አትሌቶች መካከል ይገኝበታል። ኬንያዊው አትሌት ጂኦፍሬይ ካምዎሮር የኢትዮጵያውያንን አትሌቶች ዋና ተፎካካሪ እንደሆነ የዓለም አቀፉ አትሌቲክስ ፌዴሬሽኖች ማህበር ዘገባ ያመለክታል። በሴቶች የባለፈው ዓመት የውድድሩ አሸናፊ ሜሪ ኬይታኒ የማሸነፍ የቅድሚያ ግምቱን ያገኘች ሲሆን አትሌት ሩቲ አጋ በማራቶን ውድድሩ የኬንያዊቷ አትሌት ጠንካራ ተፎካካሪ ትሆናለች ተብሎ እንደምትጠበቅም ተገልጿል። በኒው ዮርክ ማራቶን በሁለቱም ጾታዎች የሚያሸንፉ አትሌቶች የ100 ሺህ የአሜሪካን ዶላር ሽልማት የሚያገኙ ሲሆን በአጠቃላይ ለውድድሩ ተሳታፊዎች የ825 ሺህ የአሜሪካን ዶላር ተዘጋጅቷል። ለ49ኛ ጊዜ የሚካሄደው የኒው ዮርክ ማራቶን በዓለም አቀፉ አትሌቲክስ ፌዴሬሽኖች ማህበር የወርቅ ደረጃ የተሰጠው ውድድር ነው።  
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም