የዩኒቨርሲቲዎችን የምርምር ሥራዎች የጥራት ደረጃን ለማሳደግ የሕግ ማዕቀፍ እየተዘጋጀ ነው

83

መቐለ ጥቅምት 22 ቀን 2012 በዩኒቨርሲቲዎች የሚከናወኑ የምርምር ሥራዎች የጥራት ደረጃ ለማሳደግ የሕግ ማዕቀፍ እየተዘጋጀ መሆኑን የሳይንስና ከፍተኛ ትምህርት ሚኒስትር ዴኤታ ገለጹ።

ሚኒስትር ዲኤታው ፕሮፌሰር አፈወርቅ ካህሱ በዚሁ ጊዜ እንደተናገሩት ማዕቀፉ የሚዘጋጀው በዩኒቨርሲቲዎች የሚሰሩት ምርምሮች አገራዊ ፋይዳ እንዲኖራቸው ነው።

በዚህም በዩኒቨርሲቲዎች የሚሰጠው የምርምርና ማህበረሰብ አገልግሎት በሚፈለገው ደረጃና  ውጤት ለማድረስ ምርምሮቹ ወጥነት እንዲኖራቸው ይደረጋል ብለዋል።

በተመራማሪዎች የሚከናወኑ ምርምሮች እውቅና ባላቸው ጆርናሎች እንዲታተሙ እየተሰራ መሆኑንም ፕሮፌሰር አፈወርቅ አስታውቀዋል።

''የምርምር ሥራዎችን ለማከናወን የተቋማት ትስስር ያስፈልጋል'' ያሉት ሚኒስትር ዴኤታው፣ ተመራማሪዎች ከሌሎች የምርምር ተቋማት የመስራት ልምዳቸውን እንዲያሻሽሉ አሳስበዋል።

በዩኒቨርሲቲዎችእየተሰጠ ያለው የማህበረሰብ አገልግሎት እንደ ድጋፍ ሳይሆን፤ የቴክኖሎጂና የእውቀት ሽግግር ተደርጎ መታየት አለበት ብለዋል።

የመቐለ ዩኒቨርሲቲ ፕሬዚዳንት ፕሮፌሰር ክንዳያ ገብረ ሕይወት በበኩላቸው የአገሪቱ ዩኒቨርሲቲዎች ወጥነት ያለው አሰራር እንዲኖራቸው የሕግ ማዕቀፍ መዘጋጀቱ ችግር ፈቺ ምርምር ለመሥራት ያበረታታል ብለዋል።

በዩኒቨርሲቲዎች የሚከናወኑ ምርምሮችን ከኅብረተሰቡ ሕይወት ጋር ለማስተሳሰር የኢንዱስትሪ ትስስር ማጎልበትና ቴክኖሎጂ የማፍለቅ ሥራዎችን ማጠናከር ያስፈልጋል ብለዋል።

ለምርምር ስራዎች የሚውል በጀት በወቅቱ ያለመለቀቅ ችግር እየፈጠረ መሆኑን የተናገሩት የአምቦ ዩኒቨርሲቲ የምርምርና ማህበረሰብ አገልግሎት ምክትል ፕሬዚዳንት ዶክተር ብዙነሽ ሚደቅሳ ናቸው ።

በጎንደር ዩኒቨርሲቲ የምርምርና ጥናት ዳሬክተር ዶክተር ዘውዱ ተሾመ በበኩላቸው በዩኒቨርሲቲዎች ያለው የግዥ ሥርዓት ለምርምር ሥራዎች  ስለማያመች ፍተሻ እንዲደረግበት ጠይቀዋል።

የዩኒቨርሲቲዎች የምርምር ሥራዎች፣የማህበረሰብ አገልግሎት፣የኢንዱስትሪ ትስስር፣ የአሰራር ሥርዓት ማዕቀፍና የእውቀትና ቴክኖሎጂ ሽግግር የጉባዔው ዋነኛ የመወያያ አጀንዳዎች ናቸው።

በጉባዔው የመንግሥት ዩኒቨርሲቲዎች ምክትል ፕሬዚዳንቶች ፣የፌዴራል ቴክኒክና ሙያ ትምህርትና ስልጠና ኤጀንሲ፣የፌዴራል ቴክኒክ ሙያ ትምህርትና ስልጠና ኢንስቲትዩትና የአራት የግል ዩኒቨርሲቲዎች ተወካዮች በመሳተፍ ላይ ናቸው ።

በአገሪቱ ተጠሪነታቸው ለሳይንስና ከፍተኛ ትምህርት ሚኒስቴር በሆኑ 45 ዩኒቨርሲቲዎች ውስጥ 35ሺህ መምህራን እንደሚገኙ የሚኒስቴሩ መረጃ ያመለክታል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም