ኮይካ በጎፈቃደኞችን በማሰማራት ድጋፉን አጠናክሮ ይቀጥላል

82
ጥቅምት 21/2012 የኮሪያ ዓለም አቀፍ ትብብር ኤጀንሲ /ኮይካ/ በጎ ፈቃደኞችን በማሰማራት ለተቋማት የሚያደርገውን ድጋፍ አጠናክሮ እንደሚቀጥል አስታወቀ። ኤጀንሲው የበጎ ፍቃድ አገልግሎት ከሚሰጥባቸው የመንግስት ተቋማት ተወካዮች ጋር ተወያይቶ በተለይ በኢንዱስትሪ ዘርፍ በማተኮር ድጋፉን እንደሚቀጥልም ተገልጿል። በኢትዮጵያ የኮይካ ዳይሬክተር ሚስተር ኪም ዶንግሆ እንዳሉት ኤጀንሲው በኢትዮጵያ በፈረንጆቹ 1995 የተመሰረተና በአገሪቷ የኢኮኖሚና ማህበራዊ ልማት ለማምጣት ሲሰራ የቆየ ነው። በእነዚህ 24 ዓመታት ሆስፒታሎችን በመገንባት፣ የትምህርት ግብዓቶች ድጋፍ እንዲሁም የአቅም ግንባታ ስራዎችን ሲያከናውን ቆይቷል ብለዋል። ወደ ኮሪያ በመላክ ስልጠናዎች እንደሚሰጥና ይህም የኮሪያን የልማት ተሞክሮ ለመቅሰም የሚረዳ መሆኑንም ገልጸዋል። የኮሪያ በጎፈቃደኞች በኢትዮጵያ በትምህርት፣ በጤና፣ በህዝብ አስተዳደርና በገጠር ልማት ስራ እንዲሰማሩ እየተደረገ መሆኑንም አንስተዋል። በአሁኑ ወቅት 80 በጎፈቃደኞች በጤና፣ በመጀመሪያ ደረጃ ትምህርት ቤቶችና በቴክኒክና ሙያ ተቋማት እየሰሩ መሆኑንም ዳይሬክተሩ አክለዋል። ኮይካ የኮሪያን የልማት ተሞክሮዎች ለኢትዮጵያ እያጋራ መሆኑን ያነሱት ሚስተር ኪም አሁንም በተለይ በገጠር አካባቢ በኢንዱስትሪ ልማት ላይ የሚተገበሩ መርሃ ግብሮችን ለማሳደግ ይሰራል ነው ያሉት። በዚህ ዙሪያም ለተማሪዎች የቴክኒክ ስልጠና እየተሰጠ መሆኑን ጠቅሰዋል። ኮይካ መንግስት ለስራ ዕድል ፈጠራ የሰጠውን ትኩረት እንደሚደግፍና በዚሁ ላይ የተለያዩ መርሃ ግብሮችን በመቅረፅ እየሰራ መሆኑን ገልጸዋል። በቴክኒክና ሙያ ተቋማት ከክልሎች ጋር እየሰራ መሆኑንና የበጎፈቃደኞቹ ተግባር በሁለቱ አገራት መካከል ያለው ትስስር እንዲጠናከር የሚረዳ መሆኑንም ተናግረዋል። በጎፈቃደኞቹ ከአጠቃላይ አገልግሎት እስከ ከፍተኛ ባለሙያና አማካሪነት ደረጃ የሚሰሩ መሆናቸው ጠቅሰው ይህ ተግባር ተጠናክሮ እንደሚቀጥል አረጋግጠዋል። ኢትዮጵና ኮሪያ ከዲፕሎማሲ በተጨማሪ ጠንካራ የህዝብ ለህዝብ ግንኙነትም አላቸው ያሉት ደግሞ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል አቀባይ ነብያት ጌታቸው ናቸው። በኮሪያ በነበራቸው ቆይታ የአገሪቷ ዜጎች መከባበር ባህላቸው የሆኑና ለስራ ትጉህ መሆናቸውን መረዳታቸውን ገልፀዋል። በኢትዮጵያ ያሉ ተቋማት በኮይካ በኩል የሚመጡ በጎፈቃደኛ ባለሙያዎችን ልምድና ተሞክሮ አሟጠው መጠቀም እንዳለባቸው ተናግረዋል። የኮሪያን ዜጎች ተነሳሽነትና የስራ ባህል ከወረስን ስራዎቻችን ውጤታማ ማድረግ እንችላለን ብለዋል። በጎፈቃደኞቹ በየተሰማሩባቸው ተቋማት የሠራተኞች የስራ ተነሳሽነት እንዲያድግ ከማድረጋቸው በተጨማሪ የእውቀት ሽግግር እያደረጉላቸው መሆኑን አስረድተዋል።  
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም