በመቀሌ ከተማ የ14 ኪሎ ሜትር የውስጥ ለውስጥ መንገድ ግንባታ ሥራ ተጀመረ

65
መቀሌ (ኢዜአ) ጥቅምት 21 ቀን 2012 ዓ.ም ---በመቀሌ ከተማ በ100 ሚሊዮን ብር ወጪ የ14 ኪሎ ሜትር የውስጥ ለውስጥ የድንጋይ ንጣፍ መንገድ ግንባታ ሥራ ለማከናወን ወደተግባር መገባቱን የከተማው ኮንስትራክሽን፣ መንገድና ትራንስፖርት ጽህፈት ቤት አስታወቀ። በድንጋይ ንጣፍ ስራው ለመሰማራት ስልጠና የጀመሩ ወጣቶች በበኩላቸው፣ በጊዜያዊነት ከተፈጠረላቸው የሥራ ዕድል የሚያገኙትን ገንዘብ ቆጥበው ወደቋሚ ሥራ ለመሰማራት ማቀዳቸውን ተናግረዋል። የጽህፈት ቤቱ ኃላፊ አቶ ተስፋዓለም ሀዱሽ ለኢዜአ እንዳሉት የድንጋይ ንጣፍ መንገድ ሥራው በከተማው በተመደበ 100 ሚሊዮን ብር በጀት የሚከናወን ነው። በአሁኑ ወቅት ለመንገዱ የቅየሳ ሥራ የተጀመረ ሲሆን መንገዱን የሚያከናውኑ ወጣቶችም ወደ ተግባራዊ ስልጠና ገብተዋል። በመቀሌ ከሚገኙ ሰባት ክፍለከተሞች የተመለመሉ የ10ኛ፣ 12ኛ እና የኮሌጅ ትምህርታቸውን ያጠናቀቁ 1 ሺህ ወጣቶች በመንገድ ግንባታ ሥራው ጊዜያዊ የሥራ ዕድል ተጠቃሚ  እንደሚሆኑም ጠቁመዋል። እንደ አቶ ተስፋለም ገለጻ ለግንባታ ሥራው ክፍለ ከተሞች እና መንገዶችን በመለየት የቅየሳ ሥራ ተከናውኗል። ወጣቶቹ በ35 የልማት ቡድኖች ተደራጅተው ለእያንዳንዳቸው ከ400 ሜትር በላይ መንገድ በጨረታ ተሰጥቷቸዋል። በአሁኑ ወቅትም ከስልጠና ጎን ለጎን ለግንባታት የወሰዱትን መንገድ የመጥረግና የመደልደል ሥራ እያከናወኑ መሆናቸውን ነው አቶ ተስፋለም ያመለከቱት እንደኃላፊው ገለጻ ባለፉት ዓመታት በከተማው ውስጥ የድንጋይ ንጣፍ መንገድ የግንባታ ስራን በዘፈቀደ በማከናወን ይፈጠር የነበረውን የጥራት መጓደልና የጊዜ መጓተት ዘንድሮ እንዳይከሰት አስቀድሞ ለመከላከል እየተሰራ ነው። ለእዚህም ጽህፈት ቤቱ ከባለድርሻ አካላት ጋር በቅንጅት ስራውን የሚቆጣጠርና የሚከታተል ምክር ቤት እንዲቋቋም መደረጉን ነው የተናገሩት። የመንገድ ግንባታ ሥራውን ለማከናወን ተመልምለው በስልጠና ላይ ከሚገኙ የመቀሌ ከተማ ወጣቶች መካከል ወጣት መሰረት ታደሰ አንዱ ነው። ወጣቱ እንዳለው የሚያከናውኑት ሥራ በአካባቢያቸውና በክፍለከተማቸው አቅራቢያ መሆኑ በትራንስፖርት ጊዜ እንዳይባክንና ስራውን ፈጥኖ ለመጨረስ ያግዛቸዋል። "ከጊዜያዊ ሥራው የምናገኘውን ገንዘብ በመቆጠብ ወደሌላ ቋሚ ሥራ ለመሸጋጋር ከወዲሁ ዕቅድ ይዘናል " በማለትም ወጣት መሰረት አስተያየቱን ገልጿል። ቶሎ ወደስልጠና መግባታችን ቀደም ሲል በሚያዝያ እና በግንቦት ወራት ላይ የግንባታ ሥራ ዘግይቶ ሲጀመር ይከሰት የነበረውን  የመንገድ ጥራትና ብልሽት መጓደል እንደሚያስቀር የገለጸው ደግሞ የከተማው ነዋሪ ወጣት ገብረእግዚአብሔር አብርሃ ነው። "ዘንድሮ ስልጠና ወስደን ሥራውን ቶሎ መጀመራችን በግንታ መዘግየትና በጥራት መጓደው ሊደርስ የሚችለውን ኪሳራ ያስቀራል፤ ለቀጣይ ልምድም ይሆነናል" ሲል ገልጿል። ባለፈው ዓመት በመቀሌ ከተማ የተገነባው 11 ኪሎ ሜትር የውስጥ ለውስጥ መንገድን ጨምሮ እስካሁን ድረስ በከተማው 178 ኪሎ ሜትር መንገድ በድንጋይ ንጣፍ ተገንብቶ ለአገልግሎት መብቃቱን ከጽህፈት ቤቱ መረጃ ለማወቅ ተችሏል ።      
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም