ኢንጂነር ማስተዋል ስዩም የጎንደር ከተማ ተቀዳሚ ምክትል ከንቲባ ሆኑ

205
ጥቅምት 21/2012 የጎንደር ከተማ አስተዳደር ምክር ቤት ኢንጂነር ማስተዋል ስዩምን የከተማው ተቀዳሚ ምክትል ከንቲባ አድርጎ ሾመ። ምክር ቤቱ በተጨማሪም አቶ ተሾመ አግማስን በምክትል ከንቲባነት እንዲሁም ሁለት የካቢኔ አባላትን ደግሞ የገቢዎችና ሴቶች ህጻናትና ወጣቶች መምሪያ ሃላፊዎች በማድረግ ሹመታቸውን አጽድቋል። ምክር ቤቱ ሹመቱን ያጸደቀው 4ኛ ዙር 7ኛ አመት የስራ ዘመን 1ኛ አስቸኳይ ጉባኤውን ዛሬ ባካሄደበት ወቅት ነው። ምክር ቤቱ የአዲሱን ከንቲባ ሹመት በሙሉ ድምጽ ያጸደቀው በትምህርት ዝግጅታቸው በረጅም አመታት የስራ ልምዳቸውና ህዝቡን በቅንነትና በታማኝነት ለማገልገል ያላቸውን ዝግጁነት ከገመገመ በኋላ ነው። አዲሱ ተቀዳሚ ምክትል ከንቲባ በኢንጂነሪንግ ዘርፍ በተለያዩ የሙያና የሃላፊነት ቦታዎች ላለፉት 17 አመታት የሰሩ ሲሆን በጎንደር ዩንቨርሲቲ የቴክኖሎጂ ፋከልቲም በመምህርነትና በዲንነት ያገለገሉ ናቸው። አዲሱ ተቀዳሚ ምክትል ከንቲባ በቅርቡ የክልሉ ባህልና ቱሪዝም ቢሮ ሃላፊ በመሆን የተሾሙትን ዶክተር ሙሉቀን አዳነን በመተካት የተሾሙ ናቸው። በምክትል ከንቲባነት የተሾት አቶ ተሾመ አግማስ በበኩላቸው የመጀመሪያና ሁለተኛ ዲግሪ የትምህርት ዝግጅት ያላቸው ሲሆን ላለፉት 12 አመታት በተለያዩ የስራ ሃላፊነት ቦታዎች አገልግለዋል። ምክር ቤቱ በተጨማሪም አቶ ሃይለሚካኤል አለባቸውን የከተማው ገቢዎች መምሪያ ሃላፊ እንዲሁም ወይዘሪት ውብአካል ቢራራን ደግሞ የከተማው ሴቶች ህጻናትና ወጣቶች መምሪያ ሃላፊ በመሆን እንዲያገለግሉ ሹመታቸውን አጽድቋል። ኢንጂነር ማስተዋል ስዩም በምክር ቤቱ ፊት የቃለ መሃላ ስነ-ስርአት ከፈጸሙ በኋላ ባደረጉት ንግግር ጎንደር ከተማን ወደ ቀደመ ገናና ስሟና ክብሯ ለመመለስ ህዝቡና ምክር ቤቱ የጣለባቸውን ሃላፊነት ለመወጣት ቃል ገብተዋል። በተለይም በከተማው የሚታየውን ስራ አጥነት፤ የመኖሪያ ቤት እጦት፤ የመሰረተ ልማትና የመልካም አስተዳደር ጥያቄዎችን ደረጃ በደረጃ ለመፍታት ትኩረት ሰጥተው እንደሚሰሩ አረጋግጠዋል። የከተማዋን የቱሪስት ፍሰት ለሚያሳድጉና የኢንቨስትመንት እንቅስቃሴውን ለሚያጎለብቱ ተግባራት ቅድሚያ በመስጠት ሰላምና ደህንነቷን ወደ ተሻለ ደረጃ ለማድረስ የተጠናከረ ጥረት እንደሚያደርጉም አስታውቀዋል። ምክር ቤቱ በውሎው ለቀጣዮቹ 10 አመታት የሚያገለግለውን የከተማዋን መዋቅራዊ ፕላን ለማሻሻል በባለሙያዎች ተጠንቶ የቀረበውን ሰነድ ተወያይቶ ስራ ላይ እንዲውል አቅጣጫ አስቀምጧል። ለቀድሞው የከተማው ተቀዳሚ ምክትል ከንቲባ የተዘጋጀውን የፋሲል ግንብ ቅርጽ የመታሰቢያ ስጦታ በአዲሱ ተቀዳሚ ምክትል ከንቲባ እጅ ምክር ቤቱ እንዲበረከትላቸው አድርጓል።    
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም