በምስራቅ ጎጃም ዞን ግብአት ወቅቱን ጠብቆ ባለመቅረቡ መቸገራቸውን አርሶ አደሮች ገለፁ

57
ደብረ ማርቆስ ሰኔ 12/2010 በምስራቅ ጎጃም ዞን ማዳበሪያ በወቅቱ ባለመቅረቡ የመኸር እርሻ ስራችን እየተስተጓጎለ ነው ሲሉ አርሶ አደሮች ቅሬታቸውን ገለፁ። የዞኑ ግብርና መምሪያ በበኩሉ ለመኸር እርሻ ከሚያስፈልገው ከአንድ ሚሊዮን 214 ሺህ 600 ኩንታል ማዳበሪያ ውስጥ እስካሁን ከ800 ሺህ ኩንታል በላይ ለአርሶ አደሩ መሰራጨቱን ገልጿል፡፡ የጎንቻ ሲሲ እነሴ ወረዳ የደራርጌ ቀበሌ ነዋሪ አርሶ አደር መኮንን እሸቱ እንደገለጹት በማዳበሪያ እጥረት ምክንያት በበቆሎ ሰብል ለመሸፈን ካሰቡት ግማሽ ሄክታር ማሳ ሩቡን ብቻ ነው የዘሩት። ግማሽ ሄክታር ማሳ ደግሞ በገብስ ዘር ለመሸፈን ቢያስቡም ዘር ባለማግኘታቸው ወቅቱ ያልፍብኛል የሚል ስጋት ውስጥ መሆናቸውን ተናግረዋል። በምርት ዘመኑ ከአምስት ኩንታል በላይ የአፈር ማዳበሪያ ለመግዛት ቢዘጋጁም እስካሁን አንድ ኩንታል ኤን ፒ ኤስ ቦሮን እና ግማሽ ኩንታል ዩሪያ ነው ያገኙት። የቢቩኝ ወረዳ የሬታም ቀበሌ ነዋሪ አርሶ አደር መለሰ ታረቀኝ በበኩላቸው ለ2011 የምርት ዘመን ከስምንት ኩንታል በላይ ማዳበሪያ እንደሚያስፈልጋቸው ቢያመለክቱም እስካሁን ሁለት ኩንታል ማግኘታቸውን አስታውቀዋል። በተለይ ለበቆሎ ማሳደጊያ የሚሆን ዩሪያ ማግኘት ባለመቻላቸው የሰብሉ ወቅት እያለፈበት በመሆኑ መቸገራቸውን አስታውቀዋል። በዚህ ደግሞ የምርት መጠኑ በከፍተኛ ሁኔታ ይቀንሳል የሚል ስጋት እንዳደረባቸው አስረድተዋል። የጎዛምን ወረዳ የለቅለቂታ ቀበሌ ነዋሪ አርሶ አደር ቢሻው ክብረት በበኩላቸው ከሶስት ሄክታር በላይ ለሚሆን ማሳ እስከ ሰባት ኩንታል ማዳበሪያ እንደሚያስፈልጋቸው ገልጸው፤ እስካሁን አንድ ኩንታል ተሰጥቷቸው ለበቆሎ መዝሪያ እንዳዋሉት አስታውቀዋል። የአፈር ማዳበሪያ በሚፈልጉት መጠን ባለማግኘታቸው ስንዴና ባቄላ ለመዝራት መቸገራቸውንም ጠቁመዋል። የዞኑ ግብርና መምሪያ የግብአት አቅርቦት የስራ ሂደት ባለቤት አቶ ኃይለኢየሱስ ዳምጤ ለኢዜአ እንደተናገሩት የአርሶ አደሩን ምርትና ምርታማነት ለማሳደግ የአፈር ማዳበሪያ እና የምርጥ ዘር ግብአቶችን ለማቅረብ ጥረት እየተደረገ ይገኛል። በመሆኑም በ2010/2011 የምርት ዘመን ከአንድ ሚሊዮን 214 ሺህ 600 ኩንታል በላይ ማዳበሪያ ለማቅረብ ታቅዶ እስካሁን ከ800 ሺህ ኩንታል በላይ መሰራጨቱን ተናግረዋል። ማዳበሪያው ወደ ዞኑ ቀድሞ መግባት የጀመረ ቢሆንም ወደብ ላይ ባጋጠመ የትራንስፖርት ችግር ክፍተት ተፈጥሮ እንደነበር አስረድተዋል። በዚህም ከአምስት በላይ ወረዳዎች በወቅቱ ለሚዘሩበት ሰብል እጥረት የገጠማቸው መሆኑን ጠቁመው፤ በተለይም ቀደም ሲል የተሰራጨው ማዳበሪያ በክረምት ወቅት የትራንስፖርት እጥረት ባለባቸው ወረዳዎች መላኩ በአካባቢዎች ችግሩ እንዲሰፋ አድርጓል ነው ያሉት። ይሁን እንጂ ግብአቱ እንደገባ በበቂ ሁኔታ ከደረሳቸው ወረዳዎች ችግሩን ለማቃለል በውሰት እየወሰዱ መሆኑን ገልጸዋል። ችግሩን በዘላቂነት ለመፍታትም ከክልሉ መንግስት ጋር በመነጋገር ላይ መሆናቸውን አቶ ኃይለኢየሱስ ገልጸዋል። በዞኑ በ2011 የምርት ዘመን 640 ሺህ ሄክታር በዘር የሚሸፈን ሲሆን እስካሁን 80 ሺህ ሄክታር መዝራት ተችሏል፤ በአጠቃላይ ከሚለማው መሬትም ከ23 ሚሊዮን ኩንታል በላይ ምርት ይጠበቃል።          
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም