በዓለም የባህር የውሃ መጠን መጨመር የ300 ሚሊዮን ሰዎች ህይወት ላይ ስጋት ደቅኗል-ጥናት

363

ኢዜአ፤ ጥቅምት 19/2012 በዓለም የባህር የውሃ መጠን መጨመር ለ300 ሚሊዮን ሰዎች ህይወት ስጋት መሆኑን አንድ ጥናት አመለከተ።

የግብፅ አሌክሳንድሪያ፣ የኢራቅ ሁለተኛ ግዙፍ ከተማ ባስራ ከ30 ዓመት በኋላ በውሃ ተጥለቅልቀው በባህር ሊሰጥሙ እንደሚችሉም ነው የተነገረው።

መቀመጫውን አሜሪካ ያደረገው የአየር ንብረት የጥናት ማዕከል ትናንት በ”ኔቸር ኮሙኒኬሽንስ” የምርምር መፅሔት ላይ ባሳተመው ጥናቱ የባህር የውሃ መጠን እየጨመረ መሆኑን ጠቅሷል።

በዚህም በዓለም የባህር ዳርቻዎች የሚኖሩ 300 ሚሊዮን ሰዎች በ2050 በጎርፍ ሙሉ ለሙሉ የመጥለቅለቅ አደጋ እንደሚያጋጥማቸው ስጋቱን ጠቁሟል።

የባህር ጠለል እየጨመረ መምጣቱን ተከትሎ በፈረንጆቹ 2100 ጉዳት የሚያጋጥማቸው ሰዎች ቁጥር ወደ 630 ሚለዮን ከፍ ሊል እንደሚችልም ነው ጥናቱ ያመላከተው።

የአየር ንብረት የጥናት ማዕከሉ በሚቀጥሉት 30 ዓመታት ውስጥ በባህር ዳርቻ የሚገኙት እንደ የህንድ የቢዝነስ ማዕከሏ ሙምባይ፣ የቻይናዋ ሻንጋይ እና የታይላንድ ዋና ከተማ ባንግኮክ ያሉ ከተሞች ሙሉ ለሙሉ ሊሰጥሙ እንደሚችሉ ገልጿል።

በእስያ አህጉር ብቻ በባህር ዳርቻ የሚኖሩ 237 ሚሊዮን ሰዎች በባህር የውሃ ከፍታ ምክንያት በኑሯቸው ላይ ስጋት መደቀኑን ነው ያሳያው።

የዳሰሳ ጥናቱ የአየር ንብረት ለውጥ በከተሞች፣ በኢኮኖሚ፣ በባህር ዳርቻዎች፣ በአጠቃላይ በዓለም ነባራዊ ሁኔታዎች ላይ ከፍተኛ ጫና እንደሚፈጥር ማሳየቱን ተመራማሪው ስኮት ኩልፕ ተናግረዋል።

በመሆኑም ሀገራት አፋጣምኝ መፍትሔዎችን እንዲያስቀጥሙ እና ስጋት ውስጥ ያሉ በሚሊዮን የሚቆጠሩ ዜጎቻቸውን ወደ ሌላ ቦታ እንዲያሰፍሩ ጥናቱ መክሯል።