የአይስላንድ ባለሃብቶች በኢትዮጵያ የጂኦ-ተርማልና የዓሣ ሀብት ልማት ቴክኖሎጂ ዘርፎች ቢሰማሩ የጋራ ተጠቃሚነትን ያሳድጋል ተባለ

50
ኢዜአ ጥቅምት 19 ቀን 2012 ዓም የአይስላንድ ባለሃብቶች በኢትዮጵያ የጂኦ-ተርማልና የዓሣ ሀብት ልማት ቴክኖሎጂ ዘርፎች ቢሰማሩ የሁለቱን አገሮች ህዝቦች ተጠቃሚነት ማሳደግ እንደሚቻል የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ገለጸ። የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዴኤታ አምባሳደር ዶክተር ማርቆስ ተክሌ ተቀማጭነታቸው በኡጋንዳ ካምፓላ የሆኑትን በኢትዮጰያ የአይስላድ አምባሳደር  አኑር ኦራዶቲር የሹመት ደብዳቤ ቅጅ ዛሬ ተቀብለዋል። ሚኒስትር ዴኤታው በወቅቱ እንደተናገሩት፤ ኢትዮጵያ ከአይስለንድ ጋር ያላትን ግንኙነት ይበልጥ ለማጠናከር እየሰራች ነው። አይስላንድ ባላት የካበተ የጂኦ-ተርማልና የዓሣ ሀብት ልማት ቴክኖሎጂ ባለሀብቶቿ በእነዚህ ዘርፎች በኢትዮጵያ ኢንቨስት ቢያደርጉ የሁለቱን አገሮች ህዝቦች ጥቅም ማሳደግና ግንኙነቱን ይበልጥ ማጠናከር እንደሚቻል ጠቁመዋል። አምባሳደር አኑር ኦራዶቲር በበኩላቸው ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ የ2019 የኖቤል ሰላም ተሸላሚ በመሆናቸው የተሰማቸውን ደስታ በመግለጽ ለኢትዮጵያ ህዝብና መንግስት 'የእንኳን ደስ አላችሁ' መልዕክት አስተላልፈዋል። በአምባሳደርነት ዘመናቸው የሁለቱን አገሮች ግንኙነት ይበልጥ ለማጠናከር እንደሚሰሩም ገልጸዋል። ኢትዮጵያና አይስላንድ በጥር ወር 2000 ዓ.ም በኢትዮጵያ ስምጥ ሸለቆዎች አካባቢ የጂኦ-ተርማል ሀይል ለማመንጨት የሚያስችል የትብብር ስምምነት መፈራረማቸው ይታወሳል። ስምምነቱን ተከትሎ የኢትየጵያ ኤሌክትሪክ ሃይልኮርፖሬሽን ረይክጃቪክ ጂኦ-ተርማል ከተባለ የአሜሪካና የአይስላንድ ካምፓኒ ጋር የጂኦ-ተርማል ሀይል ለማምረት የሚያስችል የአራት ቢሊዮን የአሜሪካን ዶላር ስምምነት ተፈራርሟል። በአሁኑ ሰዓት 160 የሚሆኑ ኢትዮጵያዊያን በአይስላንድ በጂኦ-ተርማል ቴክኖሎጂ የተለያዩ ስልጠናዎችን እየወሰዱ እንደሚገኙ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል አቀባይ ጽህፈት ቤት ለኢዜአ የላከው መግለጫ አመልክቷል። አይስላንድ በካምፓላ በሚገኘው ኤምባሲዋ በኩል ኢትዮጵያን ሸፍና የምትሰራ ሲሆን፤ ኢትዮጵያ ደግሞ አየርላንድ በሚገኘው ኤምባሲዋ በኩል አይስላንድን ሸፍና በመስራት ላይ ትገኛለች።  
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም