በሰርጓ ዋዜማ ተጠልፋ ወደ ዋሻ የተወሰደችው ሙሽራ የስምንት ልጆች እናት ሆነች

142
ኢዜአ፤ ጥቅምት 18/2012 በሰርጓ ዋዜማ ተጠልፋ ወደ ዋሻ የተወሰደችው ሙሽራ ግማሽ ምዕተ ዓመት ልትደፍን ጥቂት ዓመት ብቻ ቀራት። በዋሻ ኑሯዋም ስምንት ልጆችን ወልዳለች። ስፍራው ጋሹ አምባ ቀበሌ ልዩ ስሙ ጨፌ ይሰኛል፤ በአማራ ክልል ሰሜን ሸዋ ዞን ሲያደብር ና ዋዩ ወረዳ የሚገኘው ይህ ታሪካዊ ዋሻ። ከዛሬ 48 ዓመታት በፊት ከአንድ አጎራባች ጎጥ የሚኖሩ አባውራዎች ልጃቸውን ለመዳር ሽርጉድ እያሉ መሆኑን የሰማው ልጅቷን የከጀለ ጎረምሳ ሙሽራዋን ለመጥለፍ ማድባቱን ያዘ። የዛሬው የ68 ዓመቱ ሽማገሌ የወቅቱ የ20 ዓመት ጎረምሳ አቶ አጥናፉ በቀለ ከጓደኞቹ ጋር በመሆን ሙሽራዋን ወይዘሮ ዘርፌ በቀለን ለመጥለፍ ሲያጠና ከቆዬ በኋላ ቤተሰቦቿ ገበያ በሄዱበት በሰርጓ ዋዜማ በለስ ቀንቶት ሙሽራዋን ወሰደ። ሙሽራዋም የተወሰደችው እንደቤተሰቧ በግንብ በታጠረ ሌላ የገጠር ቤት ሳይሆን ተፈጥሯዊ በሆነ ዋሻ ውስጥ ወደሚኖሩ የጠላፊው ቤተሰቦች ነበር። የሰርግ ድግስም በታለመለት የዕጩ ባል ሚዜዎች ሳይሆን ቀድሞውኑ ልጅቷን ሲመኝ በነበረው የአካባቢው ጠላፊ ሚዜዎች ተበላ። "ሳይደግስ አይጣላም" እንዲሉ ለሌላ ወገን ለመዳር ዝግጅት ላይ የነበረችው ሙሽራዋ ዘርፌ በቀለ፤ እህል ውሃዋ ከጠላፊዋ ከአጥናፉ በቀለ ጋር ሆኖ ዋሻው ውስጥ ገብታ ለመደች። ለኢዜአ አስተያይታቸውን የገለጹት የወትሮዋ ሙሽራ፣ የዛሬዋ እመበለት ወይዘሮ ዘርፌም፤ ጠለፋውን ከምንም እንዳልቆጠሩት፣ ወደ ዋሻ ሲወሰዱም ምንም ፍርሃት እንዳልተሰማቸው ያስታውሳሉ። ለ48 ዓመታት በዋሻ ውስጥ ኑሯቸውን ያደረጉት ወይዘሮ ዘርፌ ና አቶ አጥናፉ ስምንት ልጆችን ወልደው፣ ኩለው የዳሩ ሲሆን 'አሁን ከላይ አንዷን ለአፈር ሰጥተናል፣ ሌሎቹ ግን በሕይወት አሉ' ይላሉ። አቶ አጥናፉ እንደሚሉት ሙሽራ ጠልፈው ያገቡበት፣ ዛሬም የሚኖሩበት የጋሽ አምባ ዋሻ ርስትነቱ በድሮ ጊዜ አቶ በቀለ ሽፈራው የሚባሉ የአካባቢው ባላባት እንደነበር ይገልጻሉ። በኋላ ለእርሳቸው ቅደመ አያት የሚሆኑ አቶ ምህረቴ የሚባሉ ሰው በነብስ ግድያ ምክንያት ከሌላ አካባቢ ወደዋሻው አስፈቅደው እንደገቡና ኑሯቸውን እንደመሰረቱም ይተርካሉ። ዛሬ ላይ በተለምዶ 'የአቶ አጥናፉ ቤት' ተብሎ የሚጠራው ይሄ ዋሻ ግን የመኖሪያ ቤትነቱ ከአቶ ምህረቴ ተጀምሮ እስከ ሰባት ትውልድ ድረስ በመኖሪያነት እያገለገለ ይገኛል። በግራና ቀኝ ወይም በስተሰሜንና በስተደቡብ ሁለት መግቢያና መውጫ ያሉት ዋሻው፤ በታች በስተምስራቅ ገደል በስተምዕራብ ደግሞ በድንጋይ የታጠረ ቁልቁለታማ ገጽታን የተላበሰ ነው። 200 ሜትር ግራ ቀኝ ስፋት እንዳለው የሚገመተው ዋሻው አሁን ላይ የአቶ አባተን ቤት ጨምሮ ሶሰት ቤቶች ዋሻው ስር ቋጥኙን ተገን በማድረግ ተሰርቷል። ቤቶቹ ውስጥ ሲገቡም ዋሻ ውስጥ ያሉ ሳይሆን ከማንኛውም የገጠር ቤት የገቡ ያህል ስሜት ይሰጣል። ከዋሻው አማካኝ ስፍራ ላይ መዳረሻው የማይታወቅ የውስጥ ለውጥ መንገድ አለው፤ አቶ አባተና ወንድማቸው በልጅነታቸው ወደውስጥ ዘልቀው ሁለት ፍየሎቻቸው ገብተው አንደቀሩ፣ ወንድማቸውና እርሳቸው ግን በአየሩ ሁኔታ ተቸግረው እንደተመለሱና በቤተሰብ እንደተቀጡ ያወሳሉ። ከዛን ጊዜ ጀምሮም  ሁለት ፍየሎችን የበላው የውስጥ ለውስጥ ዋሻ ዳግም ላይከፈት ተዘግቶ እንደቀረ ያጫወቱን አቶ አጥናፉ፤  በተለያዩ ጊዜያትም ከአካባቢው ቀሳውስት አስከ ውጭ አገር ዜጎች ዋሻው ውስጥ ለመግባት ሙከራ አድረገው እንዳልቻሉም ነግረውናል። ይህ ሰፊና ታሪካዊ ዋሻው በክፉ ዘመናትም ለበርካቶች ምስካይ ሆኖ ያገለገለ ሲሆን ለአብነትም በጠላት ወረራ ዘመን ለአርበኞች፣ በመንግስት ለውጥ ግርግር ወቅትና በክረምት ጊዜም ለአካባቢው የቁም አንስሳት መጠለያነት አገልግሏል። አቶ አጥናፉ እንዳወጉን ገና 20 ዓመት ያልሞላው ወንድ ልጃቸውን ሚስት አጋብተው ከጎናቸው ጎጆ የወጣ ሲሆን ልጁም አይኑን ባይን አይቶ ከወላጆቹ ጋር ባድማ ወርሶ መኖር ጀምሯል። ከአቶ አጥናፉ ቤተሰብ በተጨማሪ በስተሰሜን ጫፍ ከዋሻው ወጣ ብሎ ሌላ ጎረቤት ቆርቆሮ ቤት ሰርቶ በጉርብተና ይኖራሉ። ከዋሻው እንዲወጡ በተለያየ መንግስታት ጫና ተደርጎባቸው እንደነበር አውስተው፤ ዳሩ ከወሰዳችሁኝ ዋሻውንም አብራችሁ ውሰዱልኝ በሚል በእምቢታ እንደቀሩ ያውሳሉ። 'ከዋሻው ሬሳችን ይወጣል' የሚሉት ባልና ሚስቱ፤ ዋሻው ለእሳት አደጋም ሆነ ለቤት ግንባታ ወጭ ስለማይዳርግ ለመውጣት ሃሳቡም፤ ፍላቱም እንደሌላቸው ይናገራሉ። ዋሻው ከልጅነታቸው ጀምሮ በተለያዩ ሽፍቶች የከበባ ሙከራ እንደተደረገበት፣ እስካሁንም አራት ጊዜ የራስ መጠበቂያ መሳሪያ በመንግስት እንደተወሰደባቸው ና የደህንንት ስጋት እንዳለባቸው ገልጸው፤ ለዚህም መንግስት ለእርሳቸውና ለልጃቸው የጦር መሳሪያ እንዲሰጣቸው ይጠይቃሉ። የሲያደብርና ዋዩ ወረዳ የባህልና ቱሪዝም ጽህፈት ቤት ተወካይ አቶ ብዙአየሁ አባተ፣ የአቶ አጥናፉ ቤተሰብ የሚኖርበት ዋሻ ከ2009 ዓ.ም ጀምሮ ጥናት ተደርጎበት የቅርስነት መስፈርት በማሟላቱ በ2010 ዓ.ም በወረዳው ቅርስነት መመዝገቡን ገልጸዋል። ከምዝገባ በኋላ ሚዲያ ባይመለከተውም ጽህፈት ቤታቸው በበራሪ ወረቀቶች የማስተዋወቅ ስራዎች  መጀመሩንም ነው ያብራሩት። በቀጣይም ስፍራው በነዋሪዎቹ ይዞታ ስር ሆኖ የቱሪስት መዳረሻ እንዲሆንና ቤተሰቡም ሆነ የአካባቢው ማኅበረሰብም ተጠቃሚ የሚሆንበት ዕድል እንዲፈጠር እየሰራን ነው ብለዋል። አቶ አጥናፉ ከደህንነት ጋር ተያይዞ የሚያነሱት የመሳሪያ ጥያቄም እንዲሟላላቸው ይደረጋል ሲሉም አረጋግጠዋል።  
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም