ሼህ መሐመድ ቢን ዛይድ ከኢትዮጵያውያን እና ኤርትራውያን ተማሪዎች ጋር ተወያዩ

59

ኢዜአ፤ ጥቅምት 18/2012 የአቡ ዳቢ ልዑል እና የተባበሩት ዐረብ ኢምሬቶች የጦር  ኃይሎች ምክትል አዛዥ ሼህ መሐመድ ቢን ዛይድ በአገሪቱ የትምህርት ዕድል አግኝተው  የዩኒቨርሲቲ  ትምህርታቸውን እየተከታተሉ ያሉ  ኢትዮጵያውያን ና ኤርትራውያን  ተማሪዎችን ተቀብለው አነጋግረዋል።

ትላንት ለተማሪዎቹ  የእንኳን ደህና መጣችሁ መልእክት ባስተላለፉበት ወቅት፣ በሳይንስ ዘርፍ ትምህርታቸውን ለመቀጠል ለሚፈልጉ በተለይም ተሰጥኦ  ላላቸው፣ በፈጠራ ሥራ ለሚተጉ እና መሪ መሆን ለሚችሉ ተማሪዎች አገራቸው የምታደርገውን ድጋፍ አጠናክራ እንደምትቀጥልም ተናግረዋል።

ሼህ መሐመድ በዚሁ ወቅት “የላቀ ውጤት ለሚያስመዘግቡ ተማሪዎች አመቺ የትምህርት ከባቢ በመፍጠር በሳይንስ መስክ ትምህርታቸውን እንዲቀጥሉ  በማድረግ አገራቸውን እና ማኅበረሰባቸውን  ማገልገል እንዲችሉ ድጋፍ እናደርጋለን” በማለት “ሳይንስ እና ዕውቀት ለአገራት ቀጣይነት ወሳኝ  እንደሆነ እናምናለን”   በማለት ነው የገለጹት።

ተማሪዎቹ  ትምህርታቸውን ለመቀጠል እና ምኞታቸውን ለማሳካት  ሼህ መሐመድ ቢን ዛይድን ና የተባበሩት ዐረብ ኢምሬቶች ላደረጉላቸው ድጋፍ  አመስግነው ያላቸውን አድናቆትም ገልጸዋል።

በተማሪዎቹ አቀባበልና ውይይት ላይ የተለያዩ የሀገሪቱ ከፍተኛ ባለስልጣላት መገኘታቸውን የዘገበው ዘናሽናል ነው።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም